በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ተዘጋጅቶ በነበረው የወገን ለወገን የቶምቦላ ሎተሪ እጣ ባለእድለኞች ስጦታቸውን ተረከቡ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 6 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ተዘጋጅቶ በነበረው ወገን ለወገን የቶምቦላ ሎተሪ እጣ አሸናፊ ባለእድለኞች ስጦታቸውን ተረከቡ።
የቶምቦላ ሎተሪ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ሞቲ ሞረዳ በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት÷ የመጀመሪያውና ትልቁ መፈናቀል የደረሰባቸውን ወገኖች ለመታደግ በወቅቱ (ወገን ለወገን) በሚል የሎተሪ ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ስራ ተገብቷል።
በቶምቦላው ግዥ ታላቅ የህዝብ ትብብር የታየበት መሆኑን የተናገሩት አቶ ሞቲ ÷ የሽልማት አሰጣጥ ሂደቱ ቢዘገይም ፕሮጀክቱ የታለመለትን ዓላማ ከዳር ማድረሱን ተናግረዋል።
በ2010 ዓ.ም ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የክልሉ ህዝቦችን መልሶ ለማቋቋም ታልሞ በተዘጋጀው ወገን ለወገን ሎተሪ 241 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን አቶ ሞቲ ገልጸዋል።
ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ በቶምቦላ እጣው በሽልማትነት ለተካተቱ ሲኖ ትራክ፣ ሚኒባስና አይሱዙ ተሽከርካሪዎች ፣ፍሪጆችና ላፕቶፖች ግዥ 80 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉንም ነው የተናገሩት።
ቀሪው 161 ሚሊየን ብር በአስተባባሪዎቹ ባንኮች በዝግ ሂሳብ ቁጥር መቀመጡንና ለታለመለት ዓላማ የሚውል መሆኑን አስታውቀዋል።
በክልሉ የሚገኙ ዞኖችና የፋይናንስ ተቋማት እጣዎቹን ባቀዱት ልክ አለመሸጥ፣ የተሸጡትን በጊዜው ሰብስበው አለማስረከብ፣ የኮሚቴዎች መንጠባጠብና በሀገሪቱ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ደግሞ ሎተሪው እንዲዘገይ ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!