ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በተመለከተ እያሰራጩት ያለው መረጃ የተዛባ እና ሚዛናዊነት የጎደለው ነው-የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በተመለከተ እያሰራጩት ያለው መረጃ የተዛባ እና ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑን የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ አስታውቋል፡፡
መንግስት አሸባሪው የህወሓት ቡድን የጀመረውን ሀገር የማፈራርሰ ሴራ ለማክሸፍ ዜጎች ሀገራቸውን ከሽብር ቡድኑ እንዲጠብቁና የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ የራሳቸውን አፍራሽ ተልዕኮ ለማሳካት በተሳሳተ እና በተዛባ መንገድ እያሰራጩት መሆኑን ነው የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ያስታወቀው፡፡
የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ የኢትዮጵያ መንግስት ከ100 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ያስተላለፈውን የሀገርን ሉዓላዊነት የማስከበር ጥሪ መገናኛ ብዙሃኑ ለተከታዮቻቸው በተዛባ እና ሚዛናዊነት በጎደለው መልኩ ማሰራጨታቸውን አብራርቷል፡፡
በተለይም ብሉምበርግ ፣አልጀዚራ፣ዘ ጋርዲያን፣ ቢቢሲ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ሮይተርስ ፣ ፋይናንሺያል ታይምስ፣ ዎል ስትሪት ጆርናል እና አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ መግለጫውን በተዛባ እና ዋና ጭብጡን በሳተ መልኩ መዘገባቸውን ነው የገለጸው፡፡
በሌላ በኩል መገናኛ ብዙሃኑ አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች በንጹሃን ዜጎች ላይ እየፈጸመ ባለው ጭፍጨፋ እና ግድያ ዙሪያ ዝምታን መምረጣቸው አላማቸውን በግልጽ ያሳየ መሆኑን አመላክቷል፡፡
ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኑ አሸባሪው ህወሓት በሰላማዊ ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ከማጋለጥ ይልቅ ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ በተፈጠሩ ችግሮች ላይ መንግስትን መወንጀል ተያይዘውታል ነው ያለው፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!