የህወሓት ርዝራዦች ችግር እንዳይፈጥሩ እየሠራ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሻባሪው ህወሓት ርዝራዦች ወደ ክልሉ እንዳይገቡና ችግር እንዳይፈጥሩ የስጋት ቀጠናዎችን በመለየት በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ ለኢዜአ እንዳሉት ክልሉ ከአጎራባች ሱዳን ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ሰርጎ ገቦችን ለመከላከል ጥብቅ የቅንጅት ስራ እየተከናወነ ነው።
በቅርቡ በክልሉ በኩል ድንበር አቋርጠው ሊገቡ እና ሊወጡ ሲሉ በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር የዋሉ የጥፋት ቡድኑ ተላላኪዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል።
በጠረፋማ አካባቢዎች ዋነኛ የስጋት ቀጠናዎች ተለይተው ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተጠናከረ ጥበቃ እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።
የሽብር ቡድኑ የጥፋት እቅዱን ለማስፈጸም ከጉሙዝ ታጣቂ በተጨማሪ በህጋዊነት የተመዘገበ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጭምር እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
በቢሮው የሚሊሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደርጉ ሲያዳ የሽብር ቡድኑ የጥፋት ሴራ ለማክሸፍ በክልሉ ሶስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ለህብረተሰቡ ቅርብ የሆኑ የሚሊሻ አባላትን በስልጠና እና ትጥቅ ተጠናክረው የአካባቢያቸውን ደህንነት እንዲያስከብሩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!