Fana: At a Speed of Life!

በሰሜን ሸዋ ዞን የአሸባሪው ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 17 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተደረገ ሰላም ማስከበር ዘመቻ የአሸባሪው ሸኔ አባላት ከእነትጥቃቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

በዞኑ የዕዝ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አብርሃም ጋዲሣ እንደገለፁት፥ የአሸባሪው ሸኔ አባላት ከእነትጥቃቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፉት አስር ቀናት የፀጥታ ሀይሎች ተቀናጅተው ባደረጉት የፀጥታ ማስከበር ዘመቻ ነው፡፡

የሽብር ቡድኖቹ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ክላንሽኮቭ ጠብ መንጃዎች፣ የእጅ ቦምቦች፣ ሽጉጦች፣ የቡድን መሳሪያዎችና ተተኳሽ ጥይቶች መያዛቸውን አመልክተዋል፡፡

የፀጥታ አካላቱ በተጠርጣሪዎች መኖሪያ ቤቶች ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት በርካታ የፀጥታ አስከባሪዎች አልባሳት፣ ሀሰተኛ የነዋሪዎች መታወቂያና ሰነዶች መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በርካታ ፀጉረ ልውጥ ሰዎችና የአሸባሪው ሸኔ መረጃ አቀባባዮች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አሸባሪዎቹን ህወሓትና ሸኔ በመደምሰስ የሕልውና ዘመቻውን በድል ለማጠናቀቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ከሕዝብ ጋር ሆኖ በቅንጅት እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህም አሸባሪው ሸኔ ሲንቀሳቀስባቸው በነበሩ አንዳንድ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማትና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያያዊ የአገልግሎት መስጫዎች ስራ እንዲጀምሩ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ፣ ሰርጎ ገቦችን በማጋለጥና የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ባለማስተጋባት የህልውና ዘመቻውን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.