በህወሃት የሽብር ቡድን የተፈፀሙ ወንጀሎችን የማጣራት ስራ መጀመሩን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 15፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ወዲህ በህወሃት የሽብር ቡድን የተፈፀሙ ወንጀሎችን የማጣራት ስራው መጀመሩን የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 15፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ወዲህ በህወሃት የሽብር ቡድን የተፈፀሙ ወንጀሎችን የማጣራት ስራው መጀመሩን የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በፍትህ ሚኒስቴር የሚመሩ የወንጀል ምርመራ እና ማስቀጣት ቡድኖች በህወሓት የተፈጸሙትን ወንጀሎች በማጣራት አጥፊዎች በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችለውን የወንጀል ምርመራ ወንጀሎቹ የተፈጸሙበት አካባቢ በመገኘት ጀምረዋል።
ከዚህ ቀደም የሽብር ቡድኑ በመንግስት የታወጀውን የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ በመጠቀም ወረራ በፈጸመባቸው የአማራ እና አፋር ክልል ሶስት ዞኖች ላይ የፈጸማቸውን ወንጀሎች በተመለከተ በፍትህ ሚኒስቴር መግለጫ መሰጠቱ ይታወሳል።
ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከክልል ፖሊስና ከክልል ፍትህ ቢሮዎች እንዲሁም ሌሎች አጋዥ ሀይሎች የተውጣጡ አካላት የተሳተፉበት ቡድን በማዋቀር የምርመራ ስራው እንዲጀመር አድርጓል፡፡
የምርመራ ቡድኖቹም በሽብር ቡድኑ ተይዘው የነበሩና አሁን ላይ መከላከያ ሰራዊትና በሌሎች ጥምር የፀጥታ ሀይሎች ነፃ በወጡ የአፋርና የአማራ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በሽብር ቡድኑ በተፈጸመ ጥቃት በንጹሃን ሕይወት እና አካል ላይ የደረሱ ጉዳቶችን፣ የዜጎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት እና ሌሎች ጉዳቶችን እግር በእግር በመከታተል ሰፊ የምርመራ ስራ በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚሁ መሰረት ፍትህ ሚኒስቴር የሚመራው የምርመራ እና ማስቀጣት ኮሚቴ የምርመራ ስራውን ለማከናወን ያመቸው ዘንድ የወንጀል ምርመራ ቡድኖችን በማዋቀር በአፋር ክልል አንድ ቡድንና 2 ንዑሳን ቡድኖች ያሉት የምርመራ ቡድን አሰማርቷል።
በዚህም ሸዋ ሮቢትን ጨምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ስር የሚገኙ 10 ወረዳዎችን፣ በደቡብ ወሎ በሚገኙ 8 ወረዳዎችን፣ የኦሮሞ ማህበረሰብ ልዩ ዞን፣ በደሴና በኮምቦልቻ፣ ጋሸናን ጨምሮ በሰሜን ወሎ ዞን ስር ያሉ ወረዳዎችን ሸፍነው ምርመራ የሚያከናውኑ የተለያዩ የምርመራ ቡድኖችን ወደ ቦታው በመላክ አሸባሪው ቡድን የፈፀማቸውን ወንጀሎች በመመርመር ላይ ይገኛሉ፡፡
በዛሬው እለትም በዋግኽምራ እና ወልዲያ ከተሞች ተመሳሳይ የወንጀል ምርመራ የሚያካሂድ ቡድን ወደ ስፍራው ተልኳል፡፡
የተፈጸሙት ወንጀሎች ዓለም ዓቀፋዊ ወንጀሎችን የሚያቋቁሙ በመሆናቸው በሁሉም ቦታዎች የሚከናወኑት የወንጀል ምርመራዎች ዓለም ዐቀፍ መስፈርትን እንዲያሟሉ በዓለም አቀፍ የወንጀል ህግ ዙሪያ የተሻለ እውቀት እና የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን በማሳተፍ ቼክ ሊስት የማዘጋጀት ስራ ተሰርቷል፡፡
ይህም የምርመራውን ጥራት እና ወጥነት ለማስጠበቅ የሚረዳ ከመሆኑም ባለፈ ሌሎች ሀገራት የወንጀል ተሳታፊዎችን በራሳቸው ህግ እና የፍትህ ስርዓት አማካኝነት ከሰው ለማስቀጣት ወይም አሳልፈው ለዓለም ዓቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እንዲሰጡ ሲጠየቁ ትብብር የማድረግ ግዴታቸውን ሳያመነቱ እንዲወጡ ያስችላቸዋል፡፡
በዚሁ መሰረት የምርመራ ቡድኖቹ የአሸባሪው የጥፋት ቡድን የፈጸማቸውን ግድያዎች፣ የአካል ጉዳቶች፣ የዜጎች መፈናቀል፣ የወደሙ ቅርሶችን፣ የመሰረተ ልማት አውታሮች፤ የመንግስት እና የግለሰቦች ንብረቶችን፣ እና ሌሎች የፈፀማቸውን እኩይ ተግባራት በቼክ ሊስት እየተመሩ የምርመራ ስራውን ሌት ተቀን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
በተመሳሳይም በሽብር ቡድኑ ውስጥ በመሪነት በአድራጊነት፣ በአጋዥነት፣ በአነሳሽነት ወይም በሌላ ማንኛውም አይነት አቅም ደረጃ የታሳተፉ የቡድኑን አባላት ለመለየት በሚያስችል ሁኔታ በጥልቀት የሚካሄድ ሲሆን፥ በአንጻራዊነትም አጠር ያለ የምርመራ ጊዜን ተጠቅሞ ለማጠናቀቅ ተገቢው ጥረት እንደሚደረግ ገልጿል።
ጎን ለጎንም የመከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ተጠርጣሪችን በቁጥጥር ስር የማዋል እና አጥፊዎችን በፍትህ አደባባይ አቅርቦ ፍትህ የሚሰጥበትን ሁኔታ ለመፍጠር ተገቢው ስራ ይሠራል፡፡
የጥምር ሰብዓዊ መብት ጥሰት ቡድኑ ባቀረበው ምክረ ሃሳብም መሰረት በትግራይ ክልል ውስጥ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ለመመርመር የሚያስችል በቂ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን፥ አሁን በአካባቢው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት የምርመራ ሂደቱ በምን መልኩ ሊመራ እንደሚገባ በቀጣይ እየተገመገመ የሚቀጥል መሆኑንም እንገልጻለን፡፡