መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችሁ ነው” – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ለዋልያዎቹ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ33ኛው የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያዘጋጀው ይፋዊ የሽኝት መርሐ ግብር ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል።
በፕሮግራሙ ላይ በቪዲዮ የተቀረፀ መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ብሄራዊ ቡድኑ በካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ላይ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ ተመኝተዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር እና የአፍሪካ ዋንጫ መስራች ሀገር መሆኗን ያስታወሱት ፕሬዝዳንቷ በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሆነ እግር ኳስ ለመገንባት ሁሉም ሀላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።
በቪዲዮ መልዕክታቸው ላይ ፕሬዝዳንቷ ሀገራችንን ወክለው የሚሳተፉት የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ከባድ ሀላፊነት እንዳለባቸው በመጥቀስ በቡድኑ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ስም በበጎ ለማስነሳት እንዲጥሩ ጭምር አሳስበዋል።
ለብሄራዊ ቡድኑም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችሁ ነው ሲሉ ማበረታቻ ልከዋል።