የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ የታየው ቸልተኝነት ዋጋ እያስከፈለ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ የታየው ቸልተኝነት እና መዘናጋት ዋጋ እያስከፈለ መሆኑ ተገለጸ።
የኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ክትባት እና የመደበኛ ክትባት አፈጻጸም ግምገማ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ የጤና ቢሮ ሀላፊዎች፣ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ሀላፊዎች፣ አጋር አካላትና በኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ክትባት ዙሪያ እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎች በተገኙበት በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በወቅቱም፥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት እና ለመቆጣጠር ሚኒስቴሩ ከፍተኛ ግብአት በመመደብ ላለፉት ሁለት አመታት ሲሰራ እንደነበርና የመከላከያ ክትባቱንም 10 ሚሊየን ለሚጠጉ ሰዎች ማዳረስ መቻሉን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚመከሩ መከላከያ መንገዶችን ችላ በማለቱ እና ከፍተኛ መዘናጋት ውስጥ በመግባቱ በአሁኑ ጊዜ ወረርሽኙ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።
ይህም ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ህብረተሰቡ በኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ዙሪያ ግንዛቤው እንዲያሳድግና ሌሎች የጥንቃቄ መንገዶችን እንዲያከብር ጠይቀዋል።
የጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም በበኩላቸው፥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን ከገባ ጀምሮ በጤና ተቋም በተገኘ መረጃ ብቻ 6 ሺህ 800 የሚሆኑ ዜጎች ህይወታቸው ማለፉን እና በርካታ ዜጎችም ለጤና፣ ለማህበራዊ እና ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች መዳረጋቸውን አንስተዋል።
የኮቪድ-19 በሽታ ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን እና ሌሎች መከላከያ ምክሮችን ዜጎች ካለመዘናጋት እንዲጠቀሙ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እስካሁን ሲያደርጉት የነበረውን ጥረት አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
አያይዘውም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢኮንም የመደበኛ ክትባቶችም ጥሩ አፈጻጸም እንዳላቸው አንስተው፥ በተለይ የግጭት አካባቢ በነበሩ ስፍራዎች ትልቅ ስራ እንደሚጠይቅ እና በዚህ ዙሪያም በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የግምገማ መድረኩ ለተከታታይ አራት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፥ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንደሚለይበት እና ለቀጣይ ስራ ግብአት የሚገኝበት መሆኑን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!