Fana: At a Speed of Life!

በዱከም እና ገላን ከተሞች በመሬትና መሬት ነክ ዙሪያ የሚሰጠው አገልግሎት ሊሻሻል እንደሚገባ ተገልጋዮች ገለፁ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ልዩ ዞን ፊንፊኔ ዙሪያ በሚገኙት ዱከም እና ገላን ከተሞች በመሬትና መሬት ነክ ዙሪያ የሚሰጠው አገልግሎት ሊሻሻል ይገባል ሲሉ ተገልጋዮች ገልፀዋል፡፡
 
ቅሬታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያቀረቡት የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች፥ አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ተቋማቱ በሚሄዱበት ወቅት የፋይል መጥፋት እና ተያያዥ ችግሮች እንደገጠሟቸው እና ይህም ለአላስፈላጊ እንግልት እየዳረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።
 
አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማት የሚስተዋሉባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ስርዓቱን ማዘመን እና በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸውም ነው ተገልጋዮቹ የጠየቁት፡፡
 
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ባደረገው ምልከታ፥ የመሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ዙሪያ የሚሰጠውን አገልግሎት ለመታዘብ ችሏል።
 
በዚህም የሁለቱ ከተማ አስተዳደር የስራ ሃላፊዎች በመሬትና መሬት ነክ ዙሪያ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ በተገልጋዮች የተነሳው ችግር መኖሩን አምነው፥ በቀጣይ አሰራሩን ለማሻሻል እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡
 
የዱከም ከተማ ከንቲባ አቶ አብዱልጀሊል አብዱሮ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ በከተማዋ የመልካም አስተዳደር ችግር ተብለው ከተለዩት መካከል ከመሬት ነክ አገልግሎት ጋር የተገናኙት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
 
ችግሩን ለመቅረፍ የካዳስተር አገልግሎት መረጃን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ወደ አንድ ቋት የማምጣት ስራ መጀመሩን ነው የተናገሩት፡፡
 
በተመሳሳይ የገላን ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ የወይንእሸት ግዛው፥ በከተማዋ በመሬትና መሬት ነክ ዙሪያ የሚሰጠው አገልግሎት ላይ በተደጋጋሚ ቅሬታ እንደሚነሳ ጠቅሰዋል።
 
ችግሩን ለመቅረፍም 14 ሺህ የሚደርሱ ከመሬት ጋር የሚገናኙ ፋይል በከተማ አስተዳደሩ ስር መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ይህንን በአንድ ቋት ለመሰብሰብ ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።
 
እስካሁንም ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ወደ ካዳስተር ስርዓት ገብተዋል፤ በቀጣይም ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
 
በገላን ከተማ ከመሬት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ተገልጋይን በሚያጉላሉ ፈጻሚዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱም ተመላክቷል፡፡
 
 
በአዳነች አበበ
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.