Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ከ250 ሺህ ዶላር በላይ ተያዘ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ከ250 ሺህ ዶላር በላይ መያዙን የፌደራል የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩትን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች የተሰማሩ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውቋል።

የፌደራል የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ ከመደበኛ የፀጥታ ስራው በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ምቾትና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ከፍተኛ ዝግጅትና ስምሪት አድርጎ እየተቀበለ ይገኛል፡፡

ይሁንና ከትልቁ ሀገራዊ ዓላማ በተቃራኒ የግል ጥቅማቸውን ለማግበስበስ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ህገወጦች በመገኘታቸው ህገወጥ ድርጊታቸውን ለማስቆም በአዲስ አበባ በተለምዶ ኢትዮጵያ ሆቴል፣ መርካቶ እንዲሁም መሰል የጥቁር ገበያ ማዕከሎችና ሌሎች የሚጠረጠሩ አካባቢዎች በተካሄዱ ዘመቻዎች በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል መግለጫው፡፡

የከተማዋን በጎ ገፅታ ለማበላሸት በሚንቀሳቀሱ በእነዚህ ህገወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች ላይ በተወሰደ እርምጃም ከ250 ሺህ ዶላር በላይ መያዙን የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ ጠቁሟል፡፡
መግለጫው አክሎም ከህገወጥ የገንዘብ ዝውውሩ ጋር በተያያዘ ከ50 ሺህ በላይ ፓውንድ እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች እና ከ115 ሚሊየን ብር በላይ የኢትዮጵያ ገንዘብ ከተጠርጣሪዎች ጋር እጅ ከፍንጅ መያዙንም ጠቁሟል።

ከዚሁ ህገወጥ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ በተለምዶ ቤቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚኖር አንድ ተጠርጣሪ ግለሰብ ቤት ውስጥ 1 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም የሚመዝን ኦፓል እንዲሁም በከተማዋ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 በሚኖረው አማን አብደላ ዑስማን በተባለው ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ የተለያዩ ሀገራት የውጭ ገንዘቦች፣ የሞባይል ቀፎዎች፣ ትናንሽ ታብሌቶች፣ ላፕቶፖች፣ የብር ጌጣጌጦች፣ የባንክ ሂሳብ ደብተሮች እና ፍላት ቴሌቪዥኖች መያዛቸውንም ገልጿል።

በተመሳሳይም ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዘ አምስት አዘዋዋሪዎች መያዛቸውን ያመላከተው ግብረ ኃይሉ፥ የተለያዩ የተጭበረበሩ ሰነዶችን በማዘጋጀት የማጭበርበር ወንጀሎች እንዲሰሩ የሚያግዙ ሰባት ህገ-ወጥ ደላሎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጋራ ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡

በተያያዘ ሀገር በማፍረስ ሴራ ውስጥ በመሳተፍ ላይ ያሉትን የአሸባሪዎቹን የህወሓትና የሸኔ ቡድን እንቅስቃሴ በገንዘብ ሲደግፉ የነበሩ የ240 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የፋይናንስ ስርዓት እንዲቋረጥና በአካውንታቸው ውስጥ የተገኘ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲታገድ መደረጉንና ጉዳያቸውም በምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀው።

ለእንግዶች ከእንግዳ ተቀባዩ ህዝባችን ጋር በመቀናጀት ሁሉንም ነገር የተመቻቸ የማድረጉ ስራ እየተሰላጠ መሆኑን ያስታወቀው የጋራ ግብረ ኃይሉ፥ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ያለ ምንም የፀጥታ እና የደህንነት ችግር የትም ቦታ ተንቀሳቅሰው የሚፈልጉትን ለማድረግ ይችሉ ዘንድ የፌደራል የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ስምሪት መግባቱን አመላክቷል፡፡

ህብረተሰቡም በአካባቢው አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለጸጥታና ለመረጃ አካላት የተለመደ ጥቆማ መስጠቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.