ሀገራዊ የምክክር መድረክ ስኬት ሀገርን የሚያድን በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ለስኬታማነቱ ሊረባረብ ይገባል- አቶ ተስፋዬ በልጅጌ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በብዙ ሀገራት እንደሆነው፥ የፖለቲካ ስብራት አንዱ ማከሚያ፥ የሀገረ መንግስት ግንባታም አንዱ ማጽኛ መንገድ ሁሉን አካታች ሀገራዊ የምክክር መድረክ ነው።
ከፋና ብሮድሳክቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌም፥ በሀገረ መንግስት ግንባታ የረጀም ዘመን ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ በሀገራዊ ጉዳዮች መግባባት ላይ ግን ብዙ ጕድለት አለባት ይላሉ።
ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የሚታየው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ያለመያዝ ጉድለት፤ የመጨራሸው ጫፍ ላይ ደርሶ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የጣለ እስከመሆን መድረሱን ነው ያስረዱት።
በሀገር የግዛት አንድነት፣ ህገመንግስት እና ሰንደቅ ዓላማ ወጥ የሆነ አቋም የሌለባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አቶ ተስፋዬ ያነሳሉ።
አሁን የኢትዮጵያን ህልውና መታደግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን መፍታት ሀገርን ማዳን በመሆኑ፥ ሀሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር መድረክ ማዘጋጀት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን አስገዳጅም መሆኑን ሚኒስትሩ ይናገራሉ።
ከመነሻው በኢትዮጵያ በሀገር ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የዜጎች ድህንነት እና ብሄራዊ ጥቅም ላይ የጋራ መግባባት መፍጠርን ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ የያዘው መንግስት ላለፉት ሶስት አመታት አካታች ሀገራዊ የምክክር መድረክ ለመፍጠር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችን ሲያከናውን እንደነበረም ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ባለፈው ሳምንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የሀገራዊ ምክክር ኮምሽን መቋቋም የዚሁ ሂደት አካል ነው ብለዋል።
አቶ ተስፋዬ ኮምሽኑ ምን ያህል ገለለትኛ ሆኖ ይቋቋማል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም፥ በመንግስት በኩል ገለለተኛ ተቋም ለማቋቋም፤ በህግ መንግስቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠውን ኮምሽነሮችን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ የማስፀደቅ ስልጣንን ትቶ፤ የኮምሽነሮቹ ጥቆማ እና ሹመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀደቅ እስከመፍቀድ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል ብለዋል።
ይህንንም ሲያስረዱ ህግመንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እጩ ኮሚሽነሮችን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብ እንደሚችል እንደሚደነግግና የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እጩ ኮሚሽነሮችን ማቅረብ ይችላል እንደሚል አንስተዋል።
በምክክር ጊዜ ግን እጩ የማቅረብ ጉዳይ ከአስፈፃሚው እጅ ቢወጣ ኮሚሽኑን ይበልጥ ገለልተኛ ማድረግ ያስችላል ተብሎ ስለታመነበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህግ የተሰጣቸውን ስልጣን ትተው እጩ የማቅረቡ ሃላፊነት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሰጥና በአፈጉባኤው እንዲቀርቡም መወሰኑን ነው የገለፁት።
ይህም መንግስት ገለልተኛ ተቋም ለማቋቋም ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
አቶ ተስፋዬ እንዳሉት ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ የተቋቋመው ኮምሽኑ የምክክር አጀንዳዎች እና ተሳታፊዎችን በነፃነት የመምረጥ ስልጣን አለው።
እንደ እርሳቸው ገለፃ የሁሉን አካታች ሀገራዊ ምክክር መድረኩ ግብ ኢትዮጵያ በቀውስ እና አብዮት አዙሪት ውስጥ እንድትዳክር ምክንያት የሆኑ ልዩነቶችን መፍታት ነው ብለዋል።
ከዚህ በሻገር መድረኩ አሁናዊ ሁነቶችን መነሻ በማድረግ አሁናዊ ችግሮችን ለመፍታት የተቋቋመ አይደለም ብለዋል።
መንግስት፥ ኢትዮጵያን የገጠማት ችግር መላ ኢትዮጵያውያንን የሚመለከት እንደመሆኑ መጠን ችግሩንም መፍታት የሚቻለው ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል እና የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ ነው የሚል አቋም እንዳለውም ሚኒስትሩ እንሰተዋል።
መድረኩ የመንግስት ወይም የገዢው ፓርቲ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ ስኬቱ ሀገርን የሚያድን፤ ጉድለቱ ደግሞ ሀገርን በችግር ውስጥ የሚያቆይ ስለሆነ ሁሉም ዜጋ ለስኬታማነቱ መረባረብ አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
ከሳምንት በፊት በፀደቀው አዋጅ መሰረት የሀገራዊ ምክክር ኮምሽን በህዝብ ጥቆማ በሚመረጡ እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሾሞ 11 ኮምሽነሮች የሚመራ ሲሆን፥ እንድ አስፈላጊነቱ የሚራዘም የሶስት አመታት የስራ ቆይታም ይኖረዋል።
በዳዊት መስፍን
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!