አዲሱ የትብብር ማዕቀፍ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር ያላትን አጋርነት ይበልጥ ውጤታማ ያደርጋል – አቶ አህመድ ሺዴ
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ አዲሱ የዓለም ባንክ የትብብር ማዕቀፍ ኢትዮጵያ ከባንኩ ጋር ያላትን አጋርነት ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርግ ነው አሉ፡፡
ሚኒስትሩ ከዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋሊና ቪንሴሌት ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ ያላቸውን ስትራቴጂያዊ አጋርነት ማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎችና የወደፊቱን የሁለቱ ወገኖች ትብብር ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ልማት ጋር ማጣጣም በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
አቶ አህመድ ሺዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በዋናነት በተመረጡ ዘርፎች እንዲሁም በውጤት ላይ የሚያተኩረው አዲሱ የዓለም ባንክ ስትራቴጂ ኢትዮጵያ ከባንኩ ጋር ያላትን አጋርነት ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርግ ነው፡፡
የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋሊና ቪንሴሌት በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስት በኢኮኖሚ ማሻሻያው ያከናወናቸውን ተግባራትና ጠንካራ የኢኮኖሚ አስተዳደር ስራዎች አድንቀው፥ ባንኩ አጋርነቱን አጠናክሮ ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች አዲሱን የዓለም ባንክ የአጋርነት ማዕቀፍ በጋራ ማዘጋጀት አስፈላጊ ስለመሆኑ ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡