በደብረ ብርሃን የሚገኙ ፋብሪካዎች መደበኛ የምርት ሂደታቸውን በመቀጠል የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህልውና ዘመቻው ወቅት በደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ በማምረቻ ዘርፍ የተሰማሩ ሦስት የውጭ ሀገር አምራች እና አንድ የግል አልሚ ባለሐብቶች ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ገለጹ፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ክትትልና ድጋፍ መምሪያ ሃላፊ ብርሃን አለምነህ በደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ የነበሩ ኩባንያዎች የምርት ሂደታቸውን ሳያስተጓጉሉ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ሲያቀርቡ ነበር ብለዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት “ኢኬ ኩባንያ” ምርቱን ለአውሮፓ ገበያ አቅርቦ ከ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ አስገኝቷል ነው ያሉት።
በተጨማሪም “ቡርትማልት” ለሀገር ውስጥ ገበያ ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጣ ምርት ማቅረቡን ጠቁመዋል።
ኩባንያዎቹ የምርት ሂደታቸውን መቀጠላቸው ለአካባቢው ማኅበረሰብ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል ሚናው የላቀ ነው ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ አስኪያጅ የሺጥላ ሙሉጌታ እንደገለፁት፥ “ኢኬ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት”፣ “ቡርትማልት ብቅል” እና “ቺንግቻንግ” ፋብሪካዎች እስካሁን ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘታቸውን ተናግረዋል።
ከህልውና ዘመቻው ጋር ተያይዞ ጦርነቱ ወደ አካባቢው እየተቃረበ የመጣ የነበረ ቢሆንም ባለሃብቶቹ ሥራቸውን ለአፍታም ቢሆን አላቋረጡም ነው ያሉት።
ለዚህም የማኅበረሰቡ፣ የአመራሩ እና የፀጥታ ተቋማት ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ተገልጿል።
ከተቋቋመ ሁለት አመታትን ያስቆጠረው የኢንዱስትሪ ፓርኩ፥ ሥምንት ሼዶች በባለሐብቶች ተይዘው የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ሂደት ላይ ይገኛሉ።
በተያዘው በጀት አመትም ከ32 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ከተቋሙ ያገኘንው መረጃ ያመለክታል።
የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ለባለሃብቶቹ እና አስተዋፅኦ ለነበራቸው ባለድርሻ አካላት በዛሬው ዕለት ያዘጋጀው የምስጋናና የእውቅና መርሃ ግብር ተከናውኗል።
በሰላም አሰፋ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!