ክሳቸው የተቋረጠላቸው ግለሰቦች ከእስር መፈታት ለሀገራዊ የምክክር መድረክ ጠቀሜታ አለው – ምሁራን
አዲስ አበበባ፣ ጥር 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ክሳቸው የተቋረጠላቸው ግለሰቦች ከእስር መፈታት ሊካሄድ ለታሰበው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ስኬት እንደሚያግዝ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለፁ።
ሴኔጋልና ቱኒዚያን ጨምሮ በርካታ የዓለም ሀገራት ብሔራዊ ምክክር ባደረጉበት ጊዜ እስረኞችን ፈተው እንደነበርም ምሁራኑ ጠቅሰዋል።
በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና የብዙሃን ተግባቦት መምህር ደህናሰው ሽመልስ እንዳሉት÷ ብሔራዊ የውይይት መድረኩ በሀገራዊ ጉዳዮች ጥያቄ አለኝ የሚሉ አካላትን በሙሉ አሳታፊ ማድረግ ይጠበቅበታል።
ይህም በዓለም ላይ በተካሄዱ ብሄራዊ የምክክር መድረኮች ከታዩ መርሆዎች መካከል አንዱ የሆነው አካታችነትን የሚያንፀባርቅ በመሆኑ ክሳቸው እንዲቋረጥ የተደረገላቸው ግለሰቦች መፈታት ለብሔራዊ ውይይቱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የተናገሩት።
ክሳቸው በተቋረጠላቸው ግለሰቦች ከእስር መፈታት ላይ ተቃውሞ የሚያነሱ አንዳንድ አካላትም ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋትን ፓለቲካዊ አንድነትና መረጋጋር ያልተረዱ ናቸው ብለዋል።
ክሳቸው የተቋረጠላቸው ግለሰቦች ከእስር መፈታት፥ መንግስት በይቅር ባይነት ወደ ብሔራዊ የምክክር መድረኩ እያቀና ስለመሆኑ አመላካች ነው ያሉት ደግሞ÷ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ዳዊት ጉሩሙ ናቸው።
ሴኔጋልና ቱኒዚያን ጨምሮ በርካታ የዓለም ሀገራት ብሔራዊ ምክክር ባደረጉበት ጊዜ እስረኞችን ፈተው እንደነበርም አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በተመሳሳይ መንገድ ይህንን ማድረጉ ለምክክር መድረኩ ዝግጁ መሆኑን ከማሳየቱም ባሻገር ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን እንደሚቀንስም ነው ያመላከቱት፡፡
በእዮናዳብ አንዱዓለም
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!