በህወሓት የወደሙ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን መልሶ ወደ ስራ ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበረው የአማራ እና አፋር ክልሎች ያወደማቸውና ዘረፋ የፈፀመባቸውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን ጠግኖ ወደ ስራ ለመመለስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ እንዳሉት፥ በእነዚህ ክልሎች አሸባሪ ቡድኑ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የሚያወጡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን አውድሟል።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በስልክ ቆይታ ያደረጉት ሚኒስትሩ፥ የወደሙ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ከፍተኛ ገንዘብ ከመጠየቃቸው በተጨማሪ ጊዜን የሚጠይቁ ናቸው ብለዋል።
ይህ በመሆኑ እንደደረሰው ጉዳት ተቋማቱን ወደ ስራ ለመመለስ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ እቅድ በመያዝ መልሶ የማቋቋም ስራ ይሰራል ነው ያሉት።
በውሃ ተቋማቱ ላይ የደረሰው ጉዳት በባለሙያዎች በጥናት ተለይቷል ያሉት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ፥ በውሃ ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመት በመንግስት አቅም ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ ዩኒሴፍን ጨምሮ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ሆኖም ከፍተኛ ጉዳት ያልደረሰባቸው እና የሎጂስቲክ እጥረት የገጠማቸው የኮምቦልቻ ከተማን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም የውሃ ተቋማትን በፍጥነት ድጋፍ በማድረግ ወደ አገልግሎት እንዲገቡ መደረጉንም አንስተዋል።
በተጨማሪም መለስተኛ ጥገና በማድረግ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦቱን ማስቀጠል የሚቻልባቸው ከተሞች ተለይተውም ከሚኒስቴሩ እና ከክልል በተወጣጡ ባለሙያዎች ጥገና እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተደረገው ጥገና ውሃ ያገኙ አካባቢዎች መኖራቸው ተስፋ ሰጪ ናቸው ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ፥ በትናንሽ መንደሮች እና ሰዎች ተፈናቅለው በተጠለሉባቸው አካባቢዎች የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮችን በማቅረብ ዜጎች በውሃ አቅርቦት ችግር እንዳይጎዱም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በላይ ተስፋዬ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!