የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬዲዮ መቋቋም የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማሳለጥ እንደሚያገለግል ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬዲዮ ለማቋቋም የሚያስችል ጠቅላላ ጉባዔ አካሂዷል፡፡
የማህበረሰብ ሬዲዮ መቋቋሙ ዩኒቨርሲቲው የሚያካሂደውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማሳለጥ እንደሚያገለግል የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን ገልጸዋል፡፡
የምሁራንን የጥናትና ምርምር ስራዎች በማሰራጨት የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ለማሳደግ እንደሚረዳም ተናግረዋል።
የሬዲዮ ጣቢያው ግንባታ በአዲሱ የዩኒቨርሲቲው ህንፃ ላይ ተገንብቶ እየተጠናቀቀ የሚገኝ ሲሆን÷ የማሰራጫ አንቴናና የስቱዲዮ ግንባታው በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እየተካሄደ ይገኛል።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዑባህ አደም ÷ ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸውን የጥናትና ምርምር ስራዎች ለማስተዋወቅ የተለያዩ ሚዲያዎችን ሲጠቀም መቆየቱን ገልፀዋል።
ይህ አሰራር ወጪ አባካኝ ከመሆኑ ባሻገር የምርምር ስራዎችን በሚፈለገው መጠን ማሰራጨት እንዳላስቻለው ጠቁመዋል።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሬዲዮ መቋቋም እነዚህን ችግሮች በመፍታት ለተቋቋመለት ማህበረሰብ ተገቢውን አገልግሎት ይሰጣል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ።
በኢትዮጵያ 12 ዩኒቨርሲቲዎች የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ያላቸው ሲሆን፥ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያ ከዚህ በተለየ መንገድ እየተገነባ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
እዮናዳብ አንዷላም