የጥምቀት በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል-ፖሊስ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥምቀት በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲከናወን በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ፤ ለጥምቀት በዓል ሰላማዊ ክንውን ፖሊስ፣ ከተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲሁም ከወጣቶች ጋር በመቀናጀት ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
የዘንድሮው የጥምቀት በዓል አከባበር በውጭ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተገኙበት በድምቀት የሚከበር ሲሆን÷ በዓሉ የፀጥታ ስጋት ሳይኖር በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ለክብረ በዓሉ ሰላማዊ ሂደት ማህበረሰቡ እንዲሁም ወጣቶች አካባቢያቸውን በመጠበቅና ስርዓት በማስከበር የሚያደርጉትን የተለመደ ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኮማንደር ፋሲካ ጠይቀዋል።
ከከተራ ጀምሮ እስከ ጥምቀት የተጠናከረ ጥበቃ መኖሩን ተናግረው ህብረተሰቡም ሰላም በማስጠበቅ ሂደት ከፖሊስ ጋር የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ማህበረሰቡ በተለመደው መልኩ መረጃ ለመስጠት ሲፈልግ በነፃ የስልክ መስመር 991 እና በ0111 11 01 11 መደወል እንደሚችል ጠቁመው በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ፖሊስ ጣቢያዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!