ወደ ሀገር ቤት ዘመቻ አካል የሆነው የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ግብዣ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) የወደ ሀገር ቤት ዘመቻ አካል የሆነው የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ግብዣ በትላንትናው ዕለት ተካሂዷል፡፡
በታላቁ ቤተ-መንግሥት በተካሄደው የእራት መርሐ-ግብር አስቀድሞ በተካሄደ ከትኬት ሽያጭ በቀጥታ ከ800 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ገልጿል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሀገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ለመጡ ዳያስፖራዎች ምስጋናያቀረቡ ሲሆን፥ ሀገራቸውን በደንብ ተዘዋውረው እንዲመለከቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከልማት ጋር በተያያዘ ባነሱት ሃሳብ፥ ያልታዩ ፕሮጀክቶችን እንዲመለከቱ በማበረታታት ይህም ተጨማሪ ሀሳብ አመንጭተው የተሻለ ስራ ለመስራት እንደሚያስችላቸው አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
መንግስት ምንም አይነት ውሳኔዎችን ሲወስን ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮችን አስቀድሞ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ እነሱም ሉዓላዊነት፣ ብሄራዊ ጥቅምና ሀገራዊ ክብር እንደሆኑ አንስተዋል።
ማንንም ጠላት ብለን አንፈርጅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፥ ሁሉንም በአመጣጣቸው ልክ የምናስተናግደው የማንደራደርባቸውን እነዚህን ነጥቦች አስቀድመን ነውም ብለዋል፡፡
‘’በመነጋገር እናምናለን’’ ስንል ቅድመ ሁኔታን ከማስቀመጥ በፊት የሚሉትን መስማት ይቀድማል በማለት እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
ማንኛውንም ሃሳብ እንሰማለን የማይጠቅመንን እንተዋለን ወደ መስማማት የምንመጣበትን ትክክለኛ የዴሞክራሲ አካሄድ እንከተላለንም ብለዋል፡፡
ሀገርን ማቅናት የምንችለው ሰላምን የምናስፍነው በሰከነ መንገድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ምንጊዜም ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን የሚሻለውን በጋራ እንወስናለን ነው ያሉት።
የምንወስናቸው ውሳኔዎች ኢትዮጵያን ያስቀደመ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊረዳ ይገባልም ነው ያሉት፥ ይቅርታ ነገን ለማቅናት እንጂ ትናንትን ለመቀየር እንዳልሆነ ሁሉም ሊገነዘብ እንደሚገባ በማንሳት።
ጠላት ብለን የፈረጅነው ሀገር የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፥ ሆኖም ግን ፖሊሲዎቻቸው ካስቀመጥናቸው መመዘኛዎች አንጻር የማይስማሙ አንዳንድ ሀገራት አሉ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ታሪክ የሚገነዘቡ፣ ኢትዮጵያን የሚያከብሩ እና የወደፊት ተስፋዋን የሚገነዘቡ ሃገራት እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡
‘’ከእኛ ጋር ሃሳባቸው የሚስማማ ሀገራትን እናጸናለን ፤ ከእኛ ጋር ሃሳባቸው የማይስማማ ሀገራትን ደግሞ መሳሳታቸውን፣ ነጻ የነበርንና ነጻ ሆነን የምንቀጥል እና ምንም ድሃ ብንሆን በክብራችን የማንደራደር ሀገር መሆናችንን ማወቅ አለባችሁ እያልን ወደ እኛ ሃሳብ እናቀርባቸዋለን’’ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፤ እንገንባ፤ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!