በጥምቀት በዓል ወቅት የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንዲደረግ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) ከጥምቀት በዓል አከባባር ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳስቧል፡፡
ከበዓሉ አከባባር ጋር ተያይዞ ቦታዎችን የሚያስውቡ የእምነቱ ተከታዮች የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም ገልጿል፡፡
እንደሚታወቀው የጥመቀት በዓል በአደባባዮች በጣም በደማቅ ሁኔታ የሚከበርና ብዙ አማኞችና ቱሪስቶች የሚሳተፉበት ነው ያለው አገልግሎቱ፥ ለዚህም ሲባል በተለይ በከተሞች የተለያዩ የማስዋብ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አመልክቷል።
የማስዋብ ሥራው ከሚከናወንባቸው ግብዓቶች መካከል የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ናቸውም ነው የተባለው ፡፡
በየዓመቱ ከኤሌክትሪክ ንክኪ ጋር በሚፈጠር አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡
ለአከባበሩ ድምቀት የአሌክትሪክ ምሰሶዎችን በመጠቀም የሚደረጉ የማስዋብ ሥራዎች ለኤሌክትሪክ አደጋ ሊያጋልጥ ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ተቋሙ አሳስቧል፡፡
በኤሌክትሪክ ማሰራጫ ምሰሶዎች ላይ በተሽከርካሪ አደጋ የማደርስ ተግባር በበዓላት የሚሰተዋል በመሆኑ አሽከርካሪዎች ጥብቅ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ተቋሙ አመላክቷል፡፡
ህብረተሰቡ መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ የበኩልን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፥ ከኤሌክትሪክ ጋር በተገናኘ አደጋ ካጋጠመ ወይም ሌላ መረጃ ከተፈለገ ወደ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በመሄድ ማሳወቅ እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኙ ደንበኞች በነፃ የጥሪ ማዕከል 905 በመደወል ማሳወቅ እንደሚቻል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፤ እንገንባ፤ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!