ባለፉት 6 ወራት 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የሚያወጣ የምግብና መድሃኒት አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል ገብቷል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 6 ወራት 1 ነጥብ 48 ቢሊየን ብር የሚያወጣ የምግብ እና 128 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የመድሃኒት አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል መድረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለትግራይ ክልል የሕክምና ግብዓት አቅርቦቶች ድጋፍን በተመለከተ ወቅታዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ሚኒስቴሩ በመግለጫው ፥ መንግስት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ሥምምነት ላይ በደረሰበት ወቅት በትግራይ ክልል መቀሌ እና ሽሬ ጣቢያዎች ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ መድሃኒቶች እና ሌሎች የሕክምና አቅርቦቶች ማስቀመጡን ገልጿል፡፡
ከፈረንጆቹ ሰኔ ወር እስከ ታኅሣሥ 2021 ከኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ወደ ክልሉ የተላኩትን ለ 6 ወር የሚበቃ የመድሃኒቶች እና የሕክምና አቅርቦቶችን በመግለጫው እንዳካተተም ነው የጠቆመው፡፡
በተጨማሪም ከፈረንጆቹ ሐምሌ 2021 ጀምሮ በመንግስት ትብብር ፥ የተባበሩት መንግስታት የሥነ-ህዝብ ፈንድ፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን፣ ዓለምአቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት፣ ዓለም አቀፍ የሕጻናት አድን ድርጅት፣ ምግብ ለተራቡ የተሰኘ ምግባረ ሠናይ ድርጅት እና `ሲ ኤስ ቲ` 658 ሜትሪክ ቶን መድሃኒት እና የሕክምና አቅርቦቶች በ18 የጭነት መኪናዎች ወደ ክልሉ ማድረሳቸውን ነው ያመለከተው፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፥ ለድንገተኛ ሕክምና ይረዳ ዘንድ 3 ሺህ 565 ኪሎ ግራም መድሃኒቶች በአውሮፕላን ማድረሱን እና ዓለም አቀፍ የሕጻናት አድን ድርጅትም በአውሮፓ ኅብረት እርዳታ 42 የተለያዩ መድሃኒቶችን የያዙ የድንገተኛ አደጋ ሕክምና መስጫ ኪቶችን ወደ ቦታው ማድረሱንም ጠቁሟል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት 320 ካርቶን ፣ ዓለም አቀፍ የሕጻናት አድን ድርጅት 350 ካርቶን የሕይወት አድን አልሚ ምግቦች በርሃብ ለተጎዱ ሕጻናት እና ለነፍሰ-ጡሮች ይሆን ዘንድ ወደ ክልሉ መላካቸውም ነው በመግለጫው የተመለከተው፡፡
5 ሺህ 766 ሜትሪክ ቶን ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው ዓልሚ ምግቦች እና 37 ሺህ 976 ሜትሪክ ቶን የምግብ አቅርቦት ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ይከፋፈል ዘንድም ወደ ክልሉ መላኩ ተጠቁሟል፡፡
ሚኒስቴሩ ባለፈው ወር 850 ሺህ ዩኒት ክትባት በዓለም አቀፍ የሕጻናት አድን እና በዓለም ጤና ድርጅቶች ትብብር ለክልሉ ደርሷልም ነው ያለው፡፡
በርካታ ሜትሪክ ቶን የውሃ ማከሚያ ኬሚካሎች፣ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሶች፣ ማስክ እና ጓንቶች መድረሳቸውም ተመላክቷል፡፡
በመግለጫው ባለፉት 6 ወራት አጠቃላይ ግምቱ 1 ነጥብ 48 ቢሊየን ብር የሚያወጣ የምግብ እና 128 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የመድሃኒት አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል ገብቷልም ነው ያለው ሚኒስቴሩ፡፡