Fana: At a Speed of Life!

የሻዕቢያ ዋና አላማ የኢትዮጵያ አኩራፊ ሃይሎችን በማደራጀት በሀገሪቱ ሰላም እንዳይኖር ማድረግ ነው – አቶ ጌታቸው ረዳ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሻዕቢያ ዋና አላማ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አኩራፊ ሃይሎችን በማደራጀት በሀገሪቱ የተረጋጋ ሰላም እንዳይኖር ማድረግ ነው አሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመከላከያ ኮሌጅ ዓመታዊ የብሔራዊ ደህንነት ኮንፈረንስ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
አቶ ጌታቸው ረዳ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የባሕር በር ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል፡፡
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደብ የሚከለክሉበት ምክንያት ገንዘብ ስለሚጠሉ ሳይሆን ኢትዮጵያ ወደብ መጠቀም የጀመረች ዕለት የኤርትራ ወጣት መኖሪያውን ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
ይህም ኢሳያስ አላማቸውን መፈጸም የሚያስችላቸውና ሀገሪቱን እንደፈለጉ የሚገዙበትን እድል ስጋት ውስጥ የሚከት ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ የምትደቅነው ብሄራዊ የጸጥታ ስጋት የተለመደ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አኩራፊ ሃይሎችን በማደራጀት በሀገሪቱ ምንም አይነት የተረጋጋ ሰላም እንዳይኖር ማድረግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ሻዕቢያ በቀጥታ ኢትዮጵያን የመውረር ብቃት የሚኖረው የኢትየጵያ የውስጥ አቅም እንዲዳከም የጀመራቸው ሥራዎች ተጠናክረው ከቀጠሉለት ብቻ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ከዚህ ውጪ የወታደራዊ፣ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች አቅሞች እንደሌሉት ጠቁመው ÷ ችግሩን ለመቀልበስም የውስጥ ጥንካሬን ማጎልበት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ይዛ ታፍና መኖር አትችልም፤ ወደብ ያስፈልገናል፤ ለዚህም የዲፕሎማሲ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፤ ሻዕቢያን መነጠል የሚያስችል ሥራ መከወን አለበት ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ያሉት አቶ ጌታቸው÷ መከላከያ ሠራዊትም ጠንከር ላሉ የቤት ሥራዎች በሁሉም ዘርፍ ወቅቱን የዋጀ ዝግጅት ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
ወታደራዊ ዝግጅት በዋናነት ጦርነትን ማስቀረት ላይ መሆን እንዳለበት ጠቁመው ÷ በትንሽ በትልቁ ለጦርነት የመጋበዝ እድልን ማስቀረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.