የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀከት ግንባታ 84 በመቶ ደረሰ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የፕሮጀክት ግንባታ ከ84 በመቶ በላይ መድረሱን የግድቡ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ ገለጹ፡፡
ኢንጅነር ክፍሌ የግድቡ የሃይል ማመንጨት ማብሰሪያ ስነ ስርዓት ላይ እንደተናገሩት÷ የፕሮጀክቱ ሰራተኞች አመራሮች እና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች በየደረጃው ባደረጉት ብርቱ ጥረት ግድቡ ለዚህ ውጤት በቅቷል፡፡
በተለይም የፕሮጀክቱን ሂደት በየጊዜው በመከታተል፣ ድጋፍ፣ ተስፋ እና ጽናት ለሚቸሩን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ታላቅ የአክብሮት ምስጋናየን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
ግድቡ ከ163 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ጠቁመው÷ ይህም ከኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ብቻ ያለምንም የውጭ እርዳታ እና ድጋፍ የተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ዋና እና የኮሮቻ ግድብ ሲኖሩት÷ ዋናው ግድብ በ10 ነጥብ 7 ሚሊየን ሜትር ኪዩቢክ የኮንክሪት ሙሌት፤ የኮርቻ ግድቡ ደግሞ 13 ነጥብ 3 ሚሊየን በድንጋይ ሙሊት እና በኮንክሪት ልባስ የተገነባ ነው፡፡ ይህም በአለም ካሉ ታላላቅ የሃይል ማመንጫዎች ተርታ እንዲሰለፍ ያደርገገዋል ነው ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፡፡
13 ተርባይኖች በግድቡ ግርጌ እና ቀኝ በሚገኙ የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የታቀፉ ሲሆን÷ ከዋናው ግሪድ ጋር በ500 ኪሎ ቮልት እና በ400 ኪሎ ቮልት መገናኘታቸውን አብራርተዋል፡፡
ግድቡ በሚጠናቀቅበት ወቅት የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ሲሆን÷ ይህም የጣና ሃይቅ መያዝ ከሚችለው የውሃ መጠን ሁለት ተኩል ዕጥፍ የሚተልቅ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ትልቁ የሰው ሰራሽ ሃይቅ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
ግድቡ ሲሞላም ውሃው የሚተኛበት ስፍራ ከግድቡ ወደኋላ 240 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርዝመት የሚኖረው ሲሆን÷ በውስጡም ብዙ ደሴቶች እንደሚፈጠሩ ሥራ አስኪጁ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ከኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ባሻገር ለአሳ ምርት ፣ ለመዝናኛ፣ ለቱሪዝም እና ለትራንስፖርት አገልግሎት የመዋል ከፍተኛ እድሎችን ይዞ ይመጣል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በፕሮጀክቱ እስከ ከ7ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች እና ወደ 500 የሚጠጉ ከ40 ሀገራት የተውጣጡ ዜጎች እንደተሳተፉበት ተገልጿል፡፡
ግንባታው ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ወቅትም ከ10ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ተሳትፈውበታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!