የሀገር ሉዓላዊነትንና ብሔራዊ ጥቅሞችን የሚያስጠብቅ ዘመናዊ ሰራዊት ለማደራጀት ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሀገር ሉዓላዊነትንና ብሔራዊ ጥቅሞችን የሚያስጠብቅ ዘመናዊ ሰራዊት ለማደራጀት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው አሉ፡፡
የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የተደራጀ ዘመናዊ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለመገንባት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኢንስቲትዩት በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን እድገት ማስመዝገብ የቻለ ሀገራዊ ተቋም መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሀገር ሉዓላዊነትንና ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ ዘመናዊ ሰራዊት ለማደራጀት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ መታገዝ ወሳኝ መሆኑን ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ለመከላከያ ኃይል በተለይም በአየር፣ በምድርና በሳይበር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በሎጀስቲክስ፣ በስልጠና፣ በሳይበር ደህንነት፣ በመከላከያ ሰራዊት ጤና አጠባበቅ እንዲሁም በአየር ኃይልና በኤሌክትሮኒክስ ዋርፌር ዘርፎች አበይት ጉዳዮችን ያካተተ ነው።
በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራው ከፍተኛ ልዑክ የኢንስቲትዩቱን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል።