ከ102 ሺህ በላይ በሳዑዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳዑዲ አረቢያ በህገወጥ መንገድ የሚኖሩ ከ102 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በቀጣይ ሦስት ሣምንታት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ እየተሠራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
በሳዑዲ አረቢያ ከ750 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩ ሲሆን ከ450 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በህገወጥ መንገድ እንደሚኖሩ ተገልጿል።
በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት ለማስመለስ አስፈጻሚ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ ይገኛልም ነው የተባለው።
ተመላሽ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት ከመመለስ ጀምሮ እስከ ትውልድ አካባቢያቸው ድረስ የማጓጓዝ እንዲሁም በዘላቂነት የማቋቋም ስራ እንደሚካሄድ ነው በመድረኩ የተገለፀው።
የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን፣ ጤና ሚኒስቴር ፣የሥራ ክህሎት ሚኒስቴር ፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር በአጠቃላይ ከ16 በላይ የሚሆኑ ተቋማት የኮሚቴ አባል ናቸው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሳዑዲ እየተወሰዱ ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለሌሎች ሀገራት ዜጎች አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታን እየፈጠሩ መሆኑ ተመልክቷል።
በተለይም ለመኖሪያ ፍቃድ የሚጠየቀው ክፍያ ከፍተኛ መሆን፣ የቤት ኪራይ መወደድ እና በማምረቻ ፋብሪካዎች ውስጥ የኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን ቁጥር መገደብ ከባድ ሁኔታን እንደፈጠረ ተነስቷል።
በቅድስት ተሥፋዬ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!