በመዲናዋ የ100 ሺህ ቤቶች ግንባታ ሒደት በፍጥነትና ጥራት እየተከናወነ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በ2018 በጀት ዓመት ለመገንባት የታቀዱ የ100 ሺህ ቤቶች ግንባታ በፍጥነት እና በጥራት እየተከናወነ ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ከንቲባ አዳነች በገርጂ፣ ቱሉ ዲምቱ፣ ገላን ጉራ፣ አቃቂ ቃሊቲ እንዲሁም በንፋስ ስልክ ላፍቶ የገበያ ማዕከል እየተገነቡ የሚገኙ ቤቶች ያሉበትን ደረጃ ገምግመዋል፡፡
ከንቲባዋ በዚህ ወቅት ÷ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ማሟላት የከተማ አስተዳደሩ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በመዲናዋ ከፍተኛ የቤት ፍላጎት ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ከአቅርቦቱ ጋር የተጣጣመ አለመሆኑን ጠቅሰው ÷ ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት ቀን ከሌት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የ100 ሺህ ቤቶችን ግንባታ ለማከናወን ታቅዷል ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ የቤቶቹ ግንባታ በጥራትና ፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ባሳለፍነው ነሐሴ ወር አካባቢ የተጀመሩ ቤቶች በአሁኑ ወቅት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙና ይህም የሥራ ባህልን በማሳደግ የተገኘ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ በጥራት እና ፍጥነት ሌሎች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ባካተተ መልኩ እየተከናወኑ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በዚህ መሰረትም ለኑሮ ምቹ፣ የልጆች መጫዎቻ፣ የስፖርት ሜዳዎች እና ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚከወኑባቸው የጋራ መገልገያዎች እንዲኖራቸው መደረጉን አስገንዝበዋል፡፡
የግንባታ ሥራው ቀንና ሌሊት በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ÷ በተያዘው ዓመት በተለይም በመንግሥት በጀት የተጀመሩ ቤቶችን ለማጠናቀቅ እርግጠኛ ሆነናል ነው ያሉት፡፡
ለከተማዋ ነዋሪዎች የገባነውን ቃል በትክክል እየተገበርን እንገኛለን፤ ለአብነትም ባለፉት አምስት ዓመታት ከ434 ሺህ በላይ ቤቶች በከተማዋ መገንባታቸውን አብራርተዋል፡፡
ነባር የመኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች የዕድሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ያስረዱት ከንቲባዋ ÷ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ ለነባሮቹ እንዴት ማስተላለፍ እንደሚገባ ዝግጅት ተደርጓል፤ ቅድሚያም ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ