ኤች አር 6600 ረቂቅ አዋጅ እንዳይጸድቅ ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን እንዲወጣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የኮንግረስ አባላት አዘጋጅነት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል በሂደት ላይ ያለው ኤች አር 6600 ረቂቅ አዋጅ እንዳይጸድቅ ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተናገሩ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉትና በካናዳ የሚኖሩት ዮሃንስ አየለ እና ኑሮውን በአዲስ አበባ ያደረገው ወጣት መላኩ አስማማው እንዳለው÷ ረቂቅ ህጉ ባለስልጣናትን ሳይሆን በደሃው ኢትዮጵያዊ ላይ የሚያሳርፈው ጉዳት ከፍ ያለ ነውና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዚህ ልክ መንቀሳቀስ ይገባል ነው ያለው።
ወጣት መላኩ፥ በራሱ ፍላጎት ብቻ ኤች አር 6600 ከሚቃወሙ እና በውጭ ከሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ጋር ጥምረት በመፍጠር እየሰራ ነው።
ጉዳዩ መንግስትን ከመደገፍ ጋር ግንኙነት የለውም የሚለው ወጣቱ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ብቻ አስገድዶት ስለ ረቂቅ ህጉ በራሱ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ግንዛቤን እያሰፋ፤ የተቃውሞ ፊርማዎችን ዜጎች አንዲፈርሙ እያበረታታ ይገኛል።
በሌላ በኩል በካናዳ ኑሮውን ያደረገው ኢትዮጵያዊው ዮሃንስ አየለ ÷ “ዩኒቲ ፎር ኢትዮጵያ “የተባለ ስለ ኢትዮጵያ የሚያቀነቅን ማህበር አባል ሲሆን÷ ከሌሎች ወንድም አህቶቹ ጋር ኤች አር 6600 እንዳይጸድቅ የበኩሉን በመወጣት ላይ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ይህን ስራም የራሱን ዩኒቲ ፎር ኢትዮጵያን ከሌሎች ተሰሚነት ካላቸው እና በአሜሪካ ከሚገኙ ማህበራት ጋር ጥምረት ፈጥረው በመታገል ላይ ናቸው።
በአጠቃላይም የየራሳችን አመለካከቶች ፣ የፖለቲካ እንዲሁም ሌሎች እሳቤዎች ልዩነት ሊኖረን ይችላል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በዚህ ኢትዮጵያን ሊያኮስስ ከፊት በተደነቀረ የጋራ ችግር ግን አንድ መሆን ግዴታ ነው ብለዋል።
በአንዳንዶች ዘንድ ሀገር ከሚያስተዳደር አካል ጋርም ልዩነቶች ሊኖሩ ስለመቻሉ አያጠያይቅም ያሉት ወጣቶቹ መንግስትና ህዝብን በመለየት የጋራ በሚያደርገን ጉዳይ የጋራ አቋማቸንን ማሳየት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡
ስለዚህ ይህ ረቂቅ ህግ አንዳይጸድቅ ሁሉም በጋራ ሊቆም አንደሚገባ የጠየቁ ሲሆን ÷ይህን ለማድረግ ደግሞ በተለያዩ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ መካፈል እንዲሁም በቀላሉ የተቃውሞ ፊርማዎችን መፈረም ይገኝበታል ብለዋል።
በአፈወርቅ አለሙ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!