ሀሰተኛ ማህተሞችና የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች ተገኙበት የተባለ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመቱ ከተማ በህገወጥ መንገድ የተዘጋጁ ሐሰተኛ የመንግሥት ተቋማት ማሕተሞችና የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች በመኖሪያ ቤቱ አከማችቶ ተገኝቷል የተባለ አንድ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ባለቤት በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
የመቱ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ዲቪዥን ቡድን አስተባባሪ ሳጅን ኪዳኑ ዘውዱ ለኢዜአ እንደገለፁት ተጠርጣሪ ግለሰቡ ከህብረሰተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በመኖሪያ ቤቱ በተካሄደ ድንገተኛ ፍተሻ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በግለሰቡ መኖሪያ ቤት በተካሄደ ፍተሻ የመቱ ከተማ የተለያዩ ቀበሌዎችን ጨምሮ የዞን መንግስት መስሪያ ቤቶች እንዲሁም የተለያዩ ክልሎች መስሪያ ቤቶች 33 ሐሰተኛ ማሕተሞች በኤግዚቢትነት መገኘታቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኮድ 3 የሆኑ 21 የተለያዩ ሀሰተኛ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ቁጥሮች መገኘታቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።
ተጠርጣሪ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑንም ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ የወንጀል ተግባራትን ለመከላከል እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ሳጅን ኪዳኑ ጠይቀዋል።