Fana: At a Speed of Life!

በአገራዊ ምክክሩ ሁሉም ዜጋ ከግላዊ ፍላጎት በመላቀቅ ገንቢ ሚና ሊጫወት ይገባል- የጋሞ አባቶች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሀገሪቱ ዘላቂ ሠላም መረጋገጥ ሁሉም ዜጋ በአገራዊ ምክክሩ ከግል ፍላጎት በመላቀቅ ገንቢ ሚና ሊጫወት ይገባል ሲሉ የጋሞ የባህል አባቶች ተናገሩ።
የጋሞ ህዝብ የባህል አባት አቶ መንግስቱ ደምሴ በሰጡት አስተያየት፤ ሁላችንም ወደኋላ ከሚጎትቱን የጥርጣሬና ጥላቻ መንፈስ በመላቀቅ በጋራ ከምንፈልገው ደረጃ ለመድረስ በይቅርባይነትና አብሮነት የምንጓዝበትን መንገድ መገንባት ይገባናል ብለዋል።
 
ስንተማመን ኢትዮጵያን በጋራ አልምተን መጠቀም እንችላለን ያሉት አቶ መንግስቱ፥ አገራዊ የምክክር መድረኩ ለዚህ እሳቤ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።
 
ምክክሩ ኢትዮጵያዊያን እርስ በርሳችን ብሎም ከፈጣሪያችን ጋር የምንታርቅበት፤ከግል ይልቅ በጋራ የማሸነፍን ሥነ-ልቦና የምንገነባበት አገራዊ ኩነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
 
ይህን ታላቅ ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንድንችልና ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ከግለኝነት አስተሳሰብ ተላቀን ኢትዮጵያ አርቀን በማሰብ በቅንነት ልንሳተፍ ይገባል ነው ያሉት።
 
በእኛ ዘመን ያስተናገድነው ወንድምን ከወንድሙ ደም የሚያቃባ የማይጠቅም የጥላቻ አጀንዳ ማብቂያው ምዕራፍ አሁን ሊሆን ይግባል ሲሉ አመላከተዋል።
 
“ተጎድቶም ቢሆን ለዘላቂ ሠላምና አብሮነት ሲባል በይቅርታ ማለፍ የጋሞ ህዝብ በባህሉ ያዳበረው እሴት ነው” ብለዋል።
 
ተመሳሳይ እሴቶች በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ በመሆናቸው ከማይጠቅሙን ከፋፋይ አስተሳሰቦች ይልቅ አባቶቻችን በራሳችን የዘረጉልንን ባህላዊ ስርዓት ተጠቅመን ዘላቂ ሠላምና ወንድማማችነትን መገንባት ያስፈልገና ሲሉ አቶ መንግስቱ አብራርተዋል።
 
“በምክክር መድረኩ ያልተስማማንባቸው ጉዳዮች ቢኖሩ እንኳን በሂደት እየፈታን ለመሄድ መሰረት ጥለን ማለፍ አለብን” ብለዋል።
 
አሰተያየታቸውን የሰጡት ሌላው የሀገር ሽማግሌ አቶ ተፈራ ኦይቻ፥ ሀገራችን አሁን ከምትገኝበት ፈተና ወጥታ ፊቷን ወደ አንድነትና ልማት ማዞር እንድትችል የምክክር መድረኩ ቁልፍ ሚና እንዳለው ተናግራዋል።
 
በአገራዊ ምክክሩ ላይ ቅንነትንና ሆደ ሰፊነትን ይዞ በመቅረብ ኢትዮጵያን በጋራ ለማልማት የሚያስችል መፍትሔ ማበጀት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ በዚህ ላይ ለአገራዊ አንድነት ቅድሚያ በመስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
 
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ቆም ብሎ በማሰብ ኢትዮጵያ ዛሬ ለምትገኝበት ችግር ያዳረጓትን ሁኔታዎች በማጤን ከጥላቻ፣ ከፍረጃና መናናቅ ርቆ ተደጋግፎ በጋራ ማደግ የሚቻልበትን መደላድል መፍጠር እንደሚገባ አመልክተዋል።
 
የጋሞ ህዝብ ታላላቆችን የሚያከብርበትና እርስ በርስ የመደማመጥ እሴቱ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር ያለውን አብሮነት አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳስቻለው ጠቅሰው፤ መደማመጥና መከባበር የሰፈነበት ውይይት ማድረግ ለዘላቂ አገራዊ ሠላም እንደሚያስፈልግ ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
አገራዊ ምከክሩ በልሂቃን ደረጃ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀርና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በንቃት እንዲሳተፍበት ለማስቻል ከወዲሁ ቅድመ ሁኔታዎች ሊመቻች እንደሚገባም ጠቁመዋል።
 
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.