በአንዳንድ አካባቢዎች እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲቲዩት አስገነዘበ፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች እየጣለ ካለው ከባድ ዝናብ አንጻር ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል አስፈላጊ የጥንቃቄ ሥራ ሊከናወን እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡
በኢንስቲቲዩቱ የረዥም ጊዜ የአየር ጠባይ አስተባባሪ አቶ በቃሉ ታመነ÷ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎች በዋናነት የበልግ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች መሆናቸውን ገልጸው÷ እነዚህ አካባቢዎች በዓመት ከ60 እስከ 70 ከመቶ የሚሆነውን ውኃ የሚያገኙት በበልግ ወቅት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በየካቲት አጋማሽ መጀመር የነበረበት የበልግ ዝናብ ዘግይቶ መጀመሩን ጠቁመው÷ ዝናቡ በአጭር ጊዜ ሊቆም ስለሚችል ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በተለይም ከሚጥለው ዝናብ የሚገኘውን ውኃ ለእንስሳት መጠጥ ውሃ እና መኖ ለማዋል በአግባቡ መያዝ እንደሚገባም ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
በሌላ በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ መጠን ሊጨምር ስለሚችል አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ነው ያሉት።
በተለይ በከተሞች አካባቢ ቅጽበታዊ የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ከወዲሁ ማጽዳትና ማስተካከል ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!