Fana: At a Speed of Life!

የብልፅግና ፓርቲ ያዘጋጀው የህዝብ መድረክ ለኅብረተሰቡ ችግሮች ተጨባጭ መፍትሄ ለመስጠት ዕድል እንደሚፈጥር ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ ያዘጋጀው የህዝብ መድረክ ለኅብረተሰቡ ችግሮች ተጨባጭ መፍትሄ ለመስጠት ዕድል እንደሚፈጥር የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ገለጹ፡፡
ምሁራኑ ፓርቲው ለኅብረተሰብ ጥያቄዎች የማይጨበጥ ተሥፋ ከመስጠት በመቆጠብ ተጨባጭ እርምጃዎችን ወስዶ ውጤቱን ሊያሳይ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የሕገ-መንግስትና ፌደራሊዝም ትምህርት ማዕከል ዳይሬክተሩ ዶክተር ኃይለየሱስ ታዬ ÷ ውይይቱ ሀገር በመምራት ላይ ያለው ፓርቲ ወደ ህዝብ ቀርቦ ችግሮችን እንዲረዳና መፍትሄ እንዲያስቀምጥ ዕድል የሚሰጠው ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
የፖለቲካ ሣይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪው ሱራፌል ጌታሁን በበኩላቸው ÷ ከህዝብ ጋር የተደረገው ውይይት የሥራ ኃላፊዎች ከሪፖርት የዘለለ መሬት ላይ ያለውን እውነት እንዲረዱ ዕድል የሚሰጥ ነው ይላሉ፡፡
የአንዱ ክልል የፓርቲ መሪ ወደ ሌላው ክልል ሄዶ ችግሮችን ከምንጩ መስማት መቻሉ ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሄዎች መስጠት የሚያስችልና መተማመን የሚፈጥር ምህዳር መፍጠር እንዳስቻለ ምሁራኑ አንስተዋል፡፡
በውይይቶቹ የበዙ ችግሮች ከህዝቡ እየተነሱ መሆኑን የጠቀሱት ምሁራኑ ፓርቲው ከህዝቡ ችግሩን መስማቱ በበጎ የሚታይ ቢሆንም ለችግሮቹ እልባት ካልሰጠ ግን ትርጉም የለሽ እንደሚሆን ነው የሚጠቅሱት፡፡
ስለሆነም የተጠቀሱ ችግሮችን በማደራጀት ተቋማዊ አድርጎ መመለስ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
ምሁራኑ ፓርቲው በሚያደርጋቸው ውይይቶች ያልተገቡ ቃላቶችን ከመግባት ሊታቀብ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ለማኅበረሰቡ አንገብጋቢ ችግሮች ተጨባጭ መፍትሄዎች እንጂ የማይተገበሩ ተሥፋዎች አያስፈልጉም ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ መፍትሄው በገዢው ፓርቲ ብልፅግና ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ባለድርሻዎች የሚረጋገጥ ነው ብለዋል ፡፡
ህዝቡም ከመጠየቅ ባለፈ ራሱን የመፍትሄው አካል አድርጎ ማሰብ መቻል እንዳለበትም አመላክተዋል።
በአፈወርቅ እያዩ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.