የቻይናው “ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ” ለአፍሪካ ብልጽግና ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተባለ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና “ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ “ ለአፍሪካ አኅጉራዊ ዕድገት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተገለጸ፡፡
ኢኒሼቲቩ ቀጣናውን በልማት ለማሥተሳሰርና የበለጸገች አፍሪካን ዕውን ለማድረግ በከፍተኛ ደረጃ ያግዛል ነው የተባለው፡፡
በቻይና አነሳሽነት ዕውን የሚሆነው የ“ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ “ የመንገድ ፣ የባቡር ሃዲድ፣ የወደቦች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን ያካትታል ተብሏል፡፡
በኢትጵያ የእስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ኢኒስቲትዩት ከፍተኛ የዓለምአቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ አጥኚ የሆኑት አቶ መላኩ ሙሉዓለም ÷ ከአፍሪካ የ50 ዓመታት የዕድገት ዕቅዶች መካከል አህጉራዊ ትሥሥርን እውን ማድረግ ፣ ብልፅግናን ማረጋገጥ እና በአፍሪካ ዘላቂ ሠላም ማሥፈን ቀዳሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ ዕውን የሚሆነው የቻይናው “ቤልት ኤንድ ሮድ” ፕሮጀክትም ከአፍሪካ ኅብረቱ አጀንዳ 2063 ጋር የሚሰምር እና መሳ ለመሳ የሚሄድ በመሆኑ አፍሪካን እጅግ ተጠቃሚ የሚያደርግ እና የማይገኝ ዕድል ነው ብለዋል አቶ መላኩ፡፡
ከፍተኛ ባለሙያው አያይዘውም ÷ ኢትዮጵያ በ”ቤልት ኤንድ ሮድ” የልማት ፕሮጀክት የቻይና ዋነኛ አጋር ሀገር እንደመሆኗ መጠን ከጎረቤቷ ጂቡቲ ጋር በመንገድ ግንባታ፣ በባቡር ሃዲድ ዝርጋታ እና በወደቦች መሠረተ-ልማት በመተሳሰር የወጪ እና ገቢ ንግዷን በማሳለጥ ኢኮኖሚዋን እያሳደገች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ እስከ ጂቡቲ የተገነባው 752 ኪሎ ሜትር የባቡር ሃዲድም የኢትጵያን ወጭ እና ገቢ ንግድ ከማሳለጡም በላይ ኢትዮጵያ ለዓለምአቀፉ ገበያ ቅርብ እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል፡፡
የ”ቤልት ኤንድ ሮድ” ፕሮጀክት ከሃዲድ እና ከመንገድ ግንባታ በተጨማሪ ኢትዮጵያን በኢንዱስትሪ ፓርኮች መሠረተ ልማቶችም ጭምር ተጠቃሚ እንዳደረጋት ነው የሺንዋ ዘገባ ያመላከተው፡፡