Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የገነባችው የጥራት መሠረተ-ልማት ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ነው – ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ኢትዮጵያ የገነባችው ዘመናዊ የጥራት መሠረተ-ልማት የውጭ ምንዛሪ ወጪን ከመቀነስ ከመተካት ባለፈ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ነው አለ።
19ኛውን የአፍሪካ ሥነ-ልክ ድርጅት (AFRIMETS) ጠቅላላ ጉባኤ “ሥነ-ልክ ለዲጂታል ሽግግር፡ ተዓማኒ ልኬቶች ለአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ” የሚል መሪ ሐሳብ በኢትዮጵያ የጥራት መንደር ውስጥ እየተካሄደ ነው።
ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ በሚገኘው ጉባዔ ከ30 በላይ ሀገራት የተውጣጡ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተወካዮች እንዲሁም ከ8 በላይ የቴክኒክ ኮሚቴዎች በመሣተፍ ላይ ናቸው።
በጉባኤው ለአፍሪካ የልኬትና የጥራት ስርዓት እንዲሁም ለኢትዮጵያ የሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሙሉጌታ ደርበው (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ ጉባኤው ኢትዮጵያ የገነባችውን ዘመናዊ የጥራት መሠረተ-ልማት ለማስተዋወቅና ገበያ ለመፍጠር ያግዛል።
በጥራት መንደር የተገነባው ዘመናዊ የጥራት መሠረተ-ልማት ቀደም ሲል ለከፍተኛ ካሊብሬሽን፣ ለቤተ-ሙከራዎች ፍተሻ እና በውጭ ሀገራት ለሚሠጡ የጥራት ስልጠናዎች የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ወጪ በመቀነስ ረገድ ሚናው ከፍ ያለ እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ ለአፍሪካና ለቀጣናው ሀገራት ባለሙያዎች ስልጠናና አገልግሎት በመስጠት፣ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክቶችን በመወዳደር ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማምጣት ያስችለዋል ሲሉም አስረድተዋል።
የጥራት መሠረተ-ልማት አገልግሎቶች የቴክኒክ ንግድ እንቅፋቶችን በማስወገድ የኢትዮጵያ ምርቶች ድንበር ተሻጋሪ የገበያ መዳረሻ ያረጋግጣሉ ብለዋል።
እንደ ግብርና፣ የጨርቃጨርቅና የቆዳ ውጤቶች ያሉት ምርቶች በሌሎች ሀገራት ያለ ተጨማሪ ፍተሻ ቀጥታ ተቀባይነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ሁኔታ እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።
በዳንኤል አማረ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.