Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሴቶችና ሕጻናት አልሚ ምግብ ተደራሽ ለማድረግ ሥምምነት ላይ ተደረሰ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነፍሰጡር ሴቶች፣ የሚያጠቡ እናቶችንና ሕጻናት የአልሚ ምግብ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ሥምምነት ተደረሰ።

ሥምምነቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ነው ከተለያዩ ተቋማት ጋር የተፈራረመው።

ሥምምነቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነፍሰጡር ሴቶች ፣ የሚያጠቡ እናቶችና እድሜያቸው እስከ ሦስት ዓመት ለሚደርሱ ሕጻናት በመዲናዋ በሚገኙ በተለያዩ የኅብረት ሥራ ሸማቾች አማካኝነት የአልሚ ምግቦች ለማቅረብ ያስችላል ተብሏል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሃና የሺንጉስ፥ ሥምምነቱ ሕጻናት በአእምሮ እና በሥነ-ልቦና የተሻሉ እንዲሆኑ እንዲሁም በሕጻናት ላይ የሚታየውን የመቀንጨር ብሎም በእድገታቸው ላይ የሚስተዋለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመቅረፍ ያስችላል ብለዋል።

መርሃ- ግብሩን ዕውን ለማድረግ 40 ሚሊየን ብር የተመደበ ሲሆን፥ በአዲስ አበባ 11 ክፍለ ከተሞች ተግባራዊ ይሆናል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የቀዳማይ ልጅነት መርሃ-ግብር ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጃንጥራር አባይ ÷ የሚሠራጩት አልሚ ምግቦች ተገቢውን የጥራት ደረጃ የጠበቁ እንዲሆኑና ቀጣይነት ባለው መልኩ ተደራሽ እንዲሆኑ ይሠራል ብለዋል፡፡

የሸማች ማኅበራት የሚያቀርቡትን አልሚ ምግቦች አቅርቦታቸውን ሳያቆራርጡ በወቅቱ ለተጠቃሚዎች እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አሊ፤ አልሚ ምግቦች የተጠቃሚዎቹ በፍጥነት ለማቅረብ በቅንጅት እንደሚሰራ ማረጋገጣቸውን ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.