እያጋጠመ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመከላከል የሀገር ውስጥ ምርት ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣መጋቢት 30፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ እያጋጠመ ያለውን የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት ለመከላከል የሀገር ውስጥ ምርት ላይ ማተኮር እንደሚገባ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዜና መጽሔት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ በፍጆታ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መስተዋሉን ገልፀዋል፡፡
የዋጋ ግሽበቱን ለመከላከልም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቁጥጥር እና ክትትል ስራዎች ማከናወኑን ገልጸው፥ ችግሩ የአቅርቦትም በመሆኑ በቁጥጥር ብቻ የሚፈለገውን ያክል ውጤት ሊመጣ አልቻልም ብለዋል፡፡
የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ባሳደረው ተፅዕኖ ምክንያት የንግድ አቅርቦት ሰንሰለቱ በመስተጓጎሉ በተለይም በዘይት ምርት የአቅርቦት እጥረትና በስርጭት ችግር ምክንያት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መስተዋሉን ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም አንዳንድ ህገወጥ ነጋዴዎች ችግሩን እንዳባባሱት ጠቅሰው፥ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተጨማሪ ማህበረሰቡ ከመንግስት ጋር በመቀናጀት የቁጥጥር ስራውን ሊያጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
መንግስት በሀገር ውስጥ ምርት ላይ ትኩረት በማድረጉ ከውጭ ይገባ የነበረው ስንዴ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት መቆሙን የገለፁት ሚኒስትሩ፥ የዘይት ችግሩን ለመቅረፍም የሀገር ወስጥ ምርት ላይ ማተኮር እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!