የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በሁሉም አካባቢ የጸጥታ ጥበቃ ስራን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል የኦሮሚያ ክልል ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በሁሉም አካባቢ የጸጥታ ጥበቃ ስራን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል የኦሮሚያ ክልል አስታውቋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ÷ የክልሉ መንግስት ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ያካሄደውን የ3ኛ ሩብ ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ሃላፊው በመግለጫቸው፥ በእቅድ አፈጻጸሙ ጠንካራና ደካማ ጎን የተባሉ ነጥቦች መለየታቸውን አብራርተዋል፡፡
በዚህ መሰረትም በእቅድ መመራት፣ የበጀት አጠቃቀም እየተሻሻለ መምጣት፡፣ በአፈጻጸም ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ማረም መቻል ፣ አመራሩ የልማት ስራዎችን በትኩረት ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር እያጣጣመ መምራት መቻሉ እና የጸጥታ ችግሮችን በፖለቲካ ስራዎች ለመቅረፍ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በቀበሌ ደረጃና ከዛ በታች ጠንካራ የመንግስት መዋቅር መገንባት አለመቻል፣ የጸጥታ ችግር በፖለቲካ ስራዎች ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ቢሆንም በሁሉም አካባቢ በተመሳሳይ ሁኔታ አለመተግበር በደካማ ጎን መገምገሙን አንስተዋል፡፡
የመንግስት መዋቅር ለሁሉም ጉዳዮች እኩል ማንቀሳቀስ አለመቻል፣ ለአብነትም የህግ አስከባሪ አካላት የቅንጅታዊ አሰራር ልል መሆን፣ የፕሮጀክት አፈጻጸምና የገቢ አሰባሰብ ላይ ክፍተት መኖሩ እና እርስ በእርስ ለመተራረም የሚደረግ ትግል ጠንካራ አለመሆንም በግምገማው ክፍተት ተብለው የተለዩ መሆናቸው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የፖለቲካ ስራዎችን በተመለከተ በህዝብ ተሳትፎ ጠላትን ማጋለጥ፣ የጠላት አደረጃጀቶችን መመንጠር እና በየደረጃው ያለውን የመንግስት መዋቅር እና የህዝብ አደረጃጀቶችን ማጠናከር ላይ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሸኔ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ፣ በየአካባቢው የጸጥታ ጥበቃ ስራን አጠናክሮ መቀጠል እንዲሁም የጸጥታ አካላትን ማገዝና መደገፍ ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ወይም የኮምፖስት ዝግጅትን አጠናክሮ መቀጠል፣ የአፈር ማዳበሪያዎችንና ምርት ዘርን በተገቢው መንገድ ማጓጓዝ፣ የአረንጓዴ አሻራን ችግኝና የቦታ ዝግጅት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራም አንስተዋል፡፡
በይስማው አደራው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!