Fana: At a Speed of Life!

የእንቦጭን አረም ለማስወገድ የተጀመረው ዘመቻ በበጀት እጥረት እና አረሙ ባለው የመስፋፋት ባህሪ መቀጠል እንዳልቻለ ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ብቻ ይስተዋል የነበረው የእንቦጭ አረም በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች በስፋት መስተዋሉ ተገልጿል፡፡

ክልሎቹ የእንቦጭ አረሙን ለማጥፋት ጥረት ቢያደርጉም ከችግሩ ስፋት የተነሳ በአጭር ጊዜ መቆጣጠር እንዳልተቻለና ከፍ ያለ የበጀት እጥረት እንዳጋጠማቸው ነው ያመላከቱት፡፡

የፌደራል የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ፥ ችግሩ የብዙ አካላትን ርብርብ ቢጠይቅም በመንግስት በኩል የ10 ዓመት ዕቅድ ተነድፎ እንቦጭን እና መሰል አረምን በየዓመቱ 2 ሚሊየን ሄክታር ለማሰወገድ እየተሰራ ነው ብሏል፡፡

በ2008 በአማራ ክልል ጣና ሐይቅ ላይ የታየውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ ርብርቦች ቢደረጉም ፣ አረሙ ካለው የተስፋፊነት ባህሪ አንጻር አመርቂ ውጤት አልተገኘበትም ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅትም አረሙ ከአማራ ክልል አልፎ በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎችም እየተስፋፋ ነው።

ይህም በክልሎቹ ላለው የውሃ ሐብት እጅግ መቀነስ ከፍተኛ ድርሻ ስላለው አስጊ ሁኔታን የደቀነ ሆኗል።

ዶክተር አያሌው ወንዴ የጣና ሐይቅ እና ሌሎች የውሃ አካላት አስተዳዳር ስራ አሰኪያጅ ፥ ወቅታዊውን የሀገሪቱን ሁኔታ ተከትሎ በተፈጠረው አለመረጋጋት ጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም በ2014 ለማጥፋት ከመንግስት ተይዞ የነበረው 40 ሚሊየን ብር በጀት ባለመለቀቁ አረሙ ይበልጥ ሊስፋፋና ከአማራ ክልል አልፎ በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች ሊታይ ችሏል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የእንቦጭ አረሙ በኦሮሚያ ክልል ÷ በቆቃ እና ባቱ ሐይቆች፣ በደቡብ ክልል ÷ አባያ እና ጫሞ ሐይቆች በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ነው።

አረሙን ለማጥፋትም የአካባቢዎቹ ማኅበረሰቦች ጥረት ቢያደርጉም ከችግሩ ሥፋት የተነሳ ውጤቱ አጥጋቢ ሊሆን እንዳልቻለና በርካታ ሺህዎች ሄክታር የውሃ ስፋትን መውረሱን ነው የፌደራል አካበቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የገለጸው፡፡

አረሙን ለማጥፋት የአንድ ወቅት የዘመቻ ሥራ ብቻ በቂ እንዳልሆነና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የሁሉንም አካላት ርብርብ እንደሚጠይቅ ነው የተመለከተው፡፡

በሀገር ደረጃ የ10 ዓመት ዕቅድ ተይዞ በየዓመቱ 2 ሚሊየን ሄክታር እንቦጭ እና መሰል መጤ አረሞችን ለማሰወገድ ወደ ሥራ ተገብቷል ብሏል ባለስልጣኑ፡፡

በሲሳይ ጌትነት

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.