Fana: At a Speed of Life!

ከ2 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር በላይ ረቂቅ በጀት ማለት…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 56ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 2 ትሪሊየን 339 ቢሊየን 268 ሚሊየን 126 ሺህ 738 ብር ሆኖ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንዲቀርብ ወስኗል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ የወሰነው የ2019 ረቂቅ በጀት አዋጅን የተመለከቱ ሃሳቦችን ዘርዘር አድርገን እንመልከት።

👉ረቂቅ በጀቱ ከባለፈው በጀት ዓመት አንጻር…

ለ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 2 ትሪሊየን 339 ቢሊየን 268 ሚሊየን 126 ሺህ 738 ብር ሆኖ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ የተወሰነ ሲሆን÷ ይህም በባለፈው በጀት ዓመት ከተመደበው አንጻር ሲታይ በ410 ቢሊየን ብር ገደማ ብልጫ አሳይቷል።

👉በጀቱ ምን ላይ ይውላል?

በጀቱ ለመደበኛ ወጪዎች፣ ለካፒታል ወጪዎች፣ ለክልል መንግሥታት ድጋፍ እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ የሚውል ይሆናል።

በተቋማት የመንግሥትን አገልግሎት ለመስጠትና ለማሻሻል ያለመው የካፒታል ወጪ በጤና፣ በትምህርት፣ በመንገድ እና በሌሎች ዘርፎች የሚከናወኑ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን ወጪ ለመሸፈን ይውላል።

👉ረቂቅ በጀቱ ምን ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባ ነው?

ረቂቅ በጀቱ የቀረበው የ2019 የፌዴራል መንግሥት በጀት የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል የሆነው የ2019 – 2021 የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችንና የመካከለኛ ዘመን (2019 – 2023) የማክሮ ኢኮኖሚና የፊሲካል ማዕቀፍን መሰረት በማድረግ ነው።

የ2018 በጀት ዓመት የፕሮግራም በጀት አፈጻጸም መነሻ በማድረግ በቀጣይ ሊኖር የሚችለውን የማህበራዊና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎችና አላማዎች እንዲሁም በመንግሥት የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የመንግሥትን የፋይናንስ አቅም እና አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ከተሰጣቸው ተልዕኮና ኃላፊነት አንጻር የሚያስፈልገውን ወጪ በመገምገም ተዘጋጅቶ ቀርቧል።

👉ረቂቅ በጀቱ እንዴት ይጸድቃል?

ረቂቅ በጀቱ ሕጋዊነት እና የበጀት ግልጽነት በሚታይበት መልኩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት እና ክርክር ተደርጎበት ይጸድቃል።

👉ከጸደቀ በኋላ…

ይህ ከፍተኛ በጀት በታለመለት መልኩ ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲያደርግ ትግበራና እና ክትትል ላይ ከፍተኛ ትኩረትን ይሻል።

የመንግሥት ተቋማት የተፈቀዱላቸውን በጀቶች ተቀብለው የሥራ መርሐ ግብሮቻቸውን ያዘጋጃሉ፤ ይተገብራሉ።

በዚህ ወቅት የበጀት ቁጥጥር እና ክትትል ዋናው ሥራ ሲሆን በሁሉም የሕዝብ ተቋማት የፋይናንስ መለያዎች እና የአፈፃፀም ሪፖርቶች ይመረመራሉ። ይህም ገንዘቡ በትክክል ለሕዝብ ጥቅም መዋሉ የሚረጋገጥበት መንገድ ነው።

ረቂቅ በጀቱ አሁን ላይ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች በስኬት ለማጠናቀቅ ብሎም ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማስፈጽም ጉልም ሚና ይኖረዋል፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠልና በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ረቂቅ በጀቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተመልክቷል፡፡

በብርሃኑ አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.