በክልሉ በጦርነቱ የሥነ-ልቡና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሙያ ድጋፍ የሚሠጡ 1 ሺህ 200 ሰዎችን ማሠልጠን ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በጦርነት ጉዳት በደረሰባቸው አምስት ዞኖች የሥነ-ልቡና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሙያ ድጋፍ የሚያደርጉ 1 ሺህ 200 ሰዎችን ማሠልጠን ተጀመረ።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ÷ በደብረ ብርሀን ከተማ ተገኝተው ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆየውን ሥልጠና አስጀምረዋል፡፡
ሥልጠናው የሚሰጠው ጤና ሚኒስቴር እና ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ነው።
ሥልጠናው ከአምስት ዞኖች ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች እና የሃይማኖት አባቶች በደብረ ብርሀን ፣ ወልዲያ ፣ ሰቆጣና ከምቦልቻ ከተሞች ይሰጣል።
ሠልጣኞች ከሥልጠናው በኋላ በክልሉ በጦርነት ምክንያት የሥነ-ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶችና ሕጻናት ላይ ይሰራሉ ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ፥ በአማራ ክልል በተለይ ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶችና ሕጻናት በሥነ-ልቦና ለመደገፍ ፣ ለማሠልጠንና ከገቡበት ችግር እንዲወጡ ለማስቻል የባለሙያዎቹ ሥልጠና አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በአላዩ ገረመው