ከንቲባ አዳነች ከጎሮ እስከ ኮዬ ፈጬ አደባባይ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ አስጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከጎሮ መታጠፊያ እስከ ኮዬ ፈጬ አደባባይ ድረስ ያለውን አዲስ የኮሪደር ልማት ሥራ አስጀምረዋል፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ አዲሱ የኮሪደር ልማት ቀደም ሲል የለሙ መሰረተ ልማቶችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስተሳስርና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን የሚያነቃቃ ነው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም በመንገድ ላይ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ የሚፈታ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር የተገናኘ በመሆኑ ሀገራዊ ሁነቶችን ለማስተናገድ አመቺ ሁኔታን የሚፈጥርና የአካባቢውን ስታንዳርድ በእጅጉ በሚያሳድግ ሁኔታ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
የኮሪደር ልማቱ ከከተማዋ አልፎ ሀገራዊ ፋይዳ አንዳለው ጠቁመው÷ ለአካባቢው ነዋሪም ሰፊ የሥራ እድል እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
ከዚህ ቀደም በመንገድ ዙሪያ ከደረጃ በታች ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን ከፍ ባለ ደረጃ ለመስጠት በሚያስችል መልኩ በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ በትልቅ ርብርብ ይሰራል ነው ያሉት፡፡
በሥራው ውስጥ የሚሳተፉ አጠቃላይ ባለድርሻ አካላት የኮሪደር ልማቱን በትብብር፣ በፍጥነትና በጋራ እንዲያሳኩ ጥሪ አቅርበዋል።
ከጎሮ መታጠፊያ – ኮዬ ፈጬ አደባባይ የተጀመረው የኮሪደር ልማት አጠቃላይ የመንገዱ ርዝመት 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የመንገዱ ስፋት 70 ሜትር (ከነግሪነሪው ደግሞ 124 ሜትር)፣ 21 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የሳይክል መንገድ፣ 21 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና በሁለቱም በኩል 4 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት ያለው የእግረኛ መንገድ፣ ሰፊ የአረንጓዴ ሽፋን እንዲሁም የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ እንደሚኖረውም ተጠቅሷል፡፡