Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የዜግነት መርሐ ግብር ለዩክሬን ዜጎች አዘጋጃለሁ አለች

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የዜግነት መርሐ ግብር ለሁሉም የዩክሬን ዜጎች ተደራሽ እንደምታደርግ አስታውቃለች፡፡

በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የተፈረመው የዜግነት መርሐ ግብር ድንጋጌ በዩክሬን ተገንጣይ ኃይሎች ወይም ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው አካባቢዎች ብቻ የሚወሰን አይደለም ተብሏል፡፡

ይሄው የፕሬዚዳንት ፑቲን ድንጋጌ ሁሉም የዩክሬን ዜጎች በቀላሉ የሩሲያ ዜጋ ለመሆን የማመልከት መብት እንዲሰጥ የሚያዝ ስለመሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ሩሲያ ቀለል ያለ የፓስፖርት አሰጣጥ ዘዴን በአውሮፓውያኑ 2019 ለዶኔስክ እና ሉሀነስክ ተገንጣይ ኃይሎች አስተዋውቃ እንደነበር ሞሰኮ ታይምስ በዘገባው አስታውሷል፡፡

ይሄው መርሐ ግብር እስከ ግንቦት 2022 የተራዘመ ሲሆን፥ በሩሲያ በተያዘው የኬርሰን ክልል የሚኖሩ ዩክሬናውያን በሩሲያ የዜግነት መርሐ ግብር እንዲሳተፉ መደረጉ ተመላክቷል፡፡

ኪየቭ ጉዳዩን በተመለከተበሰጠችው ምላሽ፥ ሞስኮ የዩክሬን ዜጎችን ዜግነታቸውን በመንጠቅ  ዓለም አቀፍ ሕግን ጥሳለች በማለት ስትከስ ቆይታለች፡፡

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም፥ለዩክሬን ዜጎች የሌላ ሀገር ፓስፖርት መስጠት የዩክሬንን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ ደንቦችን እና መርሆዎችን መጣስ ነው ሲል አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል እየተካሄደ ባለው የሩሲያና ዩክሬን ውጊያ በዩክሬን የምዕራባውያን የሚሳኤሎች ክምችት መውደሙ ተሰምቷል፡፡

የሩስያ የጦር መርከቦች ክሩዝ ማዕከላዊ ዲኔፕሮፔትሮቭስክ ክልል የሚገኙ የጦር መሣሪያ ማከማቻዎችን በካሊበር ክሩዝ ሚሳኤሎች በመምታታቸው ከአሜሪካ የቀረበላቸውን ሚሳኤሎች ክምችት እንዳወደሙ የመከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ አስታወቋል።

በተወሰደው እርምጃ በዩናይትድ ስቴትስ የተለገሱ በርካታ ሂማር የተሰኙ የሮኬት ማስወንጨፊያዎች እና ኤም 772 ሐውዘር የተባሉ እንዲሁም የ2 ኤስ 7 ፒዮን የተሰኙ በራስ የሚንቀሳቀሱ ጠመንጃዎች ማከማቻዎች ወድመዋል ሲሉ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሌተናል ጄኔራል ኢጎር ኮናሼንኮቭ በዕለቱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር አሌክሲ ሬዝኒኮቭ በጦር ሜዳ ላይ “የጨዋታ ቀያሪ” ሲሉ ያሞካጟቻውን አራት ተጨማሪ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን ለማቅረብ አሜሪካ በዚህ ወር ቃል መግባቷን ያነሱ ሲሆን፥ ይህም ወደ ዩክሬን የተላከውን አጠቃላይ ቁጥር ወደ 12 እንደሚያደርሰው ለዎል ስትሪት ጆርናል  ገልፀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.