Fana: At a Speed of Life!

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአንድነትና የሉዓላዊነት መለኪያ ነው – አስተያየት ሰጪዎች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአንድነትና የሉዓላዊነት መለኪያ መሆኑን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

ከዚህ ባለፈም ግድቡ የኢትዮጵያውያን የትስስርና ህብረት ማሳያ በመሆኑ ህዝቦች በሃብታቸው የመጠቀም ጉዳይ በፍጹም ለድርድር የሚቀርብ አይደለም ነው ያሉት፡፡

ይህ ማለት ግን የታችኛዉ የተፋሰሱ አባል ሀገራትን ሆን ብለን እንጎዳለን ማለት አይደለምም ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ።

በሌላ በኩል በቅርብ ጊዜ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በአደራዳሪነት የቀረቡትም ሆኑ የጉዳዩ ባለቤት ነን የሚሉ አካላት የመረጡት መንገድ የተሳሳተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከታዛቢነት አልፈው እንደ ጉዳይ ባለቤት የሆኑት ሀገራት እንዴትና በምን አግባብ ወደ እንዲህ አይነቱ ዳኝነት ሊገቡ እንደቻሉ በዓለም አቀፍ ህግ ሊጠየቁ ይገባልም ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚችለውን ተሳትፎ እያደረገበት ባለው ግድብ ላይ የሚኖር የውጭ አካላት ተፅእኖ ተቀባይነት እንደሌለውም አውስተዋል፡

በአንጻሩ ድርድሩ ላይ የተንፀባረቁት አቋሞች እነማን በምን መንገድ ለመሄድ እንዳሰቡ የሚያመላክቱና ለኢትዮጵያ ደግሞ የተሻለ ነገር እያመጣ እንዳለም አንስተዋል።

ጦርነትን አማራጭ የሚያደርጉ አካላት ጉዳዩን ሊያጤኑት እንደሚገባ ያሳሰቡት አስተያየት ሰጪዎች፥ ግብጽ ለኢትዮጵያ የአባይ ገባርና ምንጮች የምትችለውን ትብብርና ድጋፍ ብታደርግ የተሻለ ተጠቃሚ እንደምትሆንም ያነሳሉ።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዘር፣ በቀለም፣ ብሄር እና ኃይማኖት ሳይለያይ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ከፍጻሜ ለማድረስ መረባረብ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ዜጎች በጉጉት የሚናፍቁትን ስኬት እውን ለማድረግ በገንዘብም ይሁን ሌሎች አስፈላጊ መስዋዕትነቶችን ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ በመክፈል የአባቶቹን ታሪክ ለመድገም በአንድነትና በህብረት መሰለፍ እንደሚኖርበት አሳስበዋል።

በመሃመድ አሊ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.