ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የለውጥ ተግባራት ውጤታማነት ጀርመን የበኩሏን ድጋፍ ታደርጋለች-አምባሳደር ስቴፋን አሁርን
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የለውጥ ተግባራት ውጤታማነት ጀርመን የበኩሏን ድጋፍ ታደርጋለች ሲሉ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አሁርን ተናገሩ፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አሁርን ጋር በሀገራቱ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ÷ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላምን በማስፈንና ልማትን በማፋጠን ረገድ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ያላቸውን ድርሻ ለማጎልበት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም እንደአገር ለሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት የጀርመን መንግስት ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሚኒስትሯ ጠይቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አሁር በበኩላቸው ÷ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሴቶችን በማብቃት፣ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሰፊው እንዲሰማሩ ለማስቻል እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የሚሰጠውን የሳይኮ ሶሻል ድጋፍ እንዲሁም መንግስት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደ ሀገር እየተካሄደ ያለውን የሪፎርም ስራ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይም በሰላም ግንባታ፣ ሴቶችን በማብቃት፣ ሰብዓዊ ድጋፎችን ተደራሽ በማድረግ፣ በታዳሽ ሀይል አቅርቦት በሌሎችም መስኮች ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው ተግባራት ጀርመን ድጋፍ እንደምታደርግ ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም በሁለቱ ወዳጅ ሀገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትኩረት እንደሚሰሩ አምባሳደሩ ቃል መግባታቸውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡