የጎሬ-ማሻ-ቴፒ መንገድ ግንባታ አፈፃፀም ከ35 በመቶ በላይ የደረሰ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን ከኦሮሚያ እና ከጋምቤላ ክልሎች ጋር በአቋራጭ የሚያስተሳስረው የጎሬ-ማሻ-ቴፒ መንገድ ግንባታ አፈፃፀም ከ35 በመቶ በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የመንገድ ግንባታው በትኩረት እየተሰራ መሆኑንና በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ወደ አስፋልት ማንጠፍ ሥራ እንደሚሸጋገር ተገልጿል፡፡
140 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ፕሮጀክቱ፥ በእስከአሁኑ የግንባታ ሂደት የአፈር ጠረጋና ሙሌት፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ፣ የሰብቤዝ ንጣፍ፣ የጠጠር መፍጨት እና የነባር መንገድ ለትራፊክ ምቹ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
የመንገዱ የጎን ስፋት ትከሻን ጨምሮ በዞኑ ከተማ 21 ነጥብ 5 ሜትር፣ በወረዳ 19 ሜትር እና በገጠር 10 ሜትር መሆኑ ተመላክቷል።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ መንግስትና በኮሪያው ኤግዚም ባንክ ወጪ እንደሚሸፈንም ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ቀድሞ ይወስድ የነበረውን ከ6 እስከ 8 ሰዓት የጉዞ ጊዜ በግማሽ ያሳጥረዋል ተብሏል።
በተጨማሪም ከአዲስ አበባ በጅማ – መቱ አድርጎ ጋምቤላ የሚዘልቀውን አውራ ጎዳና እና ከአዲስ አበባ – በጅማ -ሚዛን ቴፒ የሚሄደውን ሌላ ዋና መንገድ በአቋራጭ የሚያስተሳስር ሲሆን፥ የኢሉአባቦር እና የሸካ ዞኖችንም በቅርበት በማቆራኘት የጎላ ሚና ያለው ፕሮጀክት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የመንገዱ መገንባት በአካባቢው በስፋት የሚመረቱትን የማር፥ ቡና፥ ቅመማ ቅመም እንዲሁም የሻይ ተክል ምርቶች በተገቢው ፍጥነትና ጥራት ወደ መሐል ገበያ ለማድረስና የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት ተደራሽነትንም እንደሚያሰፋ ተጠቁሟል።