የራያን ሕዝብ ህልውና ማስጠበቅ የአማራን ህልውና ማስጠበቅና የኢትዮጵያን አንድነት ማረጋገጥ ነው- ዶክተር ይልቃል ከፋለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የራያን ሕዝብ ህልውና ማስጠበቅ የአማራን ህልውና ማስጠበቅና የኢትዮጵያን አንድነት ማረጋገጥ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ፡፡
ዶክተር ይልቃል ከፋለ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷በዛሬው እለት በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ የ4ኛውን ዙር አረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውነናል ብለዋል፡፡
የራያ ሕዝብ በጀግንነት የሚታወቅ፣ በአማራነቱና በኢትዮጵያዊ አንድነቱ የማይደራደር ሕዝብ መሆኑን ጠቅሰው÷ የአማራን ሕዝብ በጠላትነት የፈረጀው ወያኔ በራያ እና አካባቢው መጠነ ሰፊ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን በርካታ ሀብት ንብረት ማውደሙን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ሰብዓዊ ጉዳትና ማህበራዊ ቀውስም አስከትሏል ነው ያሉት፡፡
በጀግናው የጸጥታ ኃይል አኩሪ ገድልና በሕዝቡ አልበገርም ባይነት አካባቢው ከጠላት ወረራ በከፊል ነፃ መሆኑን ጠቁመው÷ የራያን ሕዝብ ህልውና ማስጠበቅ የአማራን ህልውና ማስጠበቅና የኢትዮጵያ አንድነት ማረጋገጥ ነው ብለዋል።
ከጠላት ወረራ ነፃ ያልወጡ አካባቢዎችን ነፃ ለማውጣት አስፈላጊውን ትግል እናደርጋለን ያሉት ዶክተር ይልቃል÷ በወፍላ ተራሮች ላይ የተከልነው ችግኝም ትርጉሙ ብዙ እንደሆነ ጠቁመዋል።
“በጠላት የወደሙ ተቋማትን ሕዝቡን በማስተባበር መልሰን እንገነባለን፤ የወራሪውን ግፍና መከራ ተቋቁሞ በጽናት ከጀግናው የጸጥታ ኃይላችን ጋር ጠላትን ፊት ለፊት የታገለውን የራያ ሕዝብ ወደ ቀደመ የሰላምና የልማት ድባብ ለመመለስ የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር የጀመረውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል” ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!