የወለጋ ህዝብ በፍቅር የተሞላ እና ሰላም ወዳድ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የወለጋ ህዝብ በፍቅር የተሞላ እና ሰላም ወዳድ ህዝብ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በወለጋ የነበራቸውን የልማት ስራዎች ጉብኝት አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ በሶስቱም የወለጋ ዞኖች ያየኋቸው ስራዎች ተስፋ ሰጪ እና አስደሳች ናቸው ብለዋል።
ወለጋ ዛሬ ከፍተኛ የደስታ ዝናብ የሚዘንብባት ምድር ናት ሲሉ ገልጸው፤ ልማታችንን እናልማ ሰላማችንን እንጠብቅ ነው ያሉት።
የወለጋ ህዝብ በፍቅር የተሞላ እና ሰላም ወዳድ መሆኑን ገልጸው፤ ህዝቡ ጠላቱ እንኳ ቢሆን ከተቸገረ ለመርዳት ልቡ የቀና እጁ የተዘረጋ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ትምህርት፣ ዕውቀት እና ስራ የሚወደው የወለጋ ህዝብ፤ በሆነ ወቅት የሰላም እጦት ገጥሞት እንደነበር አስታውሰዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢው የልማት ስራዎች መጀመራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንበርታ፣ እንስራ፣ ለሀገር ብልጽግና በጋራ እንቁም፣ የህዝባችን አንድነት ይጠናከር ብለዋል።
በረባ ባልረባው ከመባላት፣ ከመጣላት፣ ከመዋጋት፣ አንዱ የአንደኛውን ሩጫ ከማገት እና ከማድከም በመቆጠብ በጋራ ሆነን ልማት እናረጋግጥ ሲሉ አስሳስበዋል።
የሩቅ ጠላቶች ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት መከፋፈል እና መጨቃጨቅን መተው እንደሚገባ ገልጸው፤ የጀመርነውን መልካም ጉዞ በርትተን እናስቀጥል ብለዋል።
በአቢይ ጌታሁን