Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በነሐሴ ወር መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት እንቀጥላለን አሉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከነሐሴ 1 እስከ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት መስጠታቸውን እንደሚቀጥሉ አስታወቀ፡፡

በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/13 አንቀፅ 38(2) መሰረት የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከነሐሴ 1 እስከ መስከረም 30 ባለው ጊዜ ዝግ እንደሚሆኑ ይደነግጋል፡፡

ሆኖም ወደ 2015 ዓ.ም የሚያልፉ መዝገቦችን ቁጥር ለመቀነስ፣ የበሰሉ መዝገቦችን እልባት ለመስጠት፣ እስረኛ ያለባቸውን መዝገቦች ቅድሚያ ሰጥቶ ለመስራት እንዲያስችል በዳኞች ፈቃደኝነት ላይ በመመስረት የፌዴራል ፍርድ ቤቶቹ ከነሐሴ 1 እስከ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ መደበኛውን የዳኝነት አገልግሎት መስጠታቸውን እንደሚቀጥሉ ነው ያስታወቁት ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፥ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች ያላቸውን የዕረፍት ጊዜ መስዋዕት በማድረግ መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት ፍቃደኛ በመሆናቸው ምስጋና ያቀረበ ሲሆን ፥ ተገልጋዩ በዚህ አግባብ የፍርድ ቤቶቹን አገልግሎት ማግኘት እንደሚችል ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በ2014 ዓ.ም የ12 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ከዓለም አቀፍ የፍርድ ቤቶች ውጤታማነት መለኪያ መስፈርቶች አንጻር ሲታይ የውጤታማነት ደረጃው ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በዚህም የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ፣ ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በአማካይ 90 ከመቶ የሚሆኑ ጉዳዮች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉም ተነስቷል፡፡

የወንጀል ጉዳዮችን በተመለከተ እስረኛ ያለባቸው መዛግብት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እልባት እንዲያገኙ እየተሰራ እንደሚገኝም ከኢትዮጵያ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.