Fana: At a Speed of Life!

“ሀሮሜ”፣ በኦሮሚያ ክልል ለአርሶ አደሮች ምቹና ዘመናዊ መኖሪያን የመፍጠር ሒደት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት ብዙ የመልማት አቅም እያላቸውና ተረስተው የቆዩ የገጠር አካባቢዎችን በማልማት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡

ለዚህም በከተማ የተጀመረውን የኮሪደር ልማት በገጠር አካባቢዎች በመተግበር የአርሶ አደሮች የኑሮ ዘይቤ እንዲሻሻል እያደረገ ነው፡፡

የኦሮሚያ ክልል በዚሁ እሳቤ መሠረት “ሀሮሜ” በሚል ስያሜ በተሰየመ መርሐ ግብር ገጠርን ወደ ዘመናዊነት ለማሸጋገር በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡

ሀሮሜ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ገጠራማ ቀበሌዎችን የለውጥ ማዕከላት ለማድረግ የታቀደ መርሐ ግብር ነው፡፡

ሀሮሜ ፕሮግራም የግንባታ ሥራ ብቻ አይደለም፤ የልማት አስተሳሰብን መቀየርና ገጠርን ወደ አዲስ የልማት ደረጃ ማሸጋገር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ዘመናዊነት ማለት የልማት መሠረተ ልማቶችን፣ የማኅበራዊ አገልግሎቶችን፣ የፋይናንስና የፍትሕ ተቋማትን፣ ገበያን እንዲሁም አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን የምርታማነት ማዕከል ለማድረግና ወደ ሕዝቡ ማድረስን ያካትታል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ሀሮሜን ሲመሠርት፣ የመንግሥት አገልግሎት፣ መንገድ፣ ውሃ፣ ኃይል፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ጣቢያዎች፣ መድኃኒት ቤቶች፣ ባንኮችና ሌሎች አገልግሎቶችን ወደ አርሶ አደሮች መኖሪያ አካባቢ ለማድረስ ዓላማ አድርጎ ነው፡፡

ሀሮሜ በገጠር፣ በከተማና በመንግሥት መካከል ያለውን ትስስርና ግንኙነት በአዲስ መንገድ ለመገንባት ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡

የገጠር ሽግግር ማለት ግብርናን ብቻ ማሻሻል ሳይሆን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወትንም አብሮ ማሸጋገር ይጠይቃል፡፡

ገጠርን የጥሬ ዕቃ ምንጭ ብቻ አድርጎ ከመመልከት በመውጣት፣ የምርታማነት፣ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ፣ የሙያና የፈጠራ እንዲሁም የብልጽግና ማዕከላት ወደማድረግ መቀየር ያስፈልጋል፡፡

መንግሥት በርካታ የገጠር መኖሪያ አካባቢዎችን ከከፋ ችግር በማውጣት፣ በሀሮሜ አማካይነት የሕዝቡ ኑሮ እንዲለወጥ በቁርጠኝነት እየሠራ ነው፡፡

በገጠር እየተገነቡ ያሉት የሀሮሜ ቤቶች ምቹ ከመሆናቸው በላይ የአርሶ አደሩ ሀብት እየሆኑ መምጣታቸውን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በቅርቡ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

መርሐ ግብሩ በአንድ በኩል የሕዝቡን ኑሮ በማሻሻል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢንቨስትመንትና ከተማነትን በተግባር ላይ እያዋለ እንደሚገኝ ነው ያወሱት፡፡

ሀሮሜ የገጠር ሕዝብን ወደ ዘመናዊነት በማቅረብ ሁሉም ገጠራማ አካባቢዎች በልማት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉ የሚያደርግ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የተገነቡት የሀሮሜ ማዕከላት ለምረቃ እየተዘጋጁ ይገኛሉ፡፡

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.