በአማራ ክልል ስንዴን በኩታገጠም አስተራረስ ዘዴ በመዝራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው – የክልሉ ግብርና ቢሮ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ስንዴን በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በስፋት በመዝራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ አመራሮች በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ አራት አጎራባች ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኝ ከ4 ሺህ 20 ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ክላስተር ሲዘራ የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሀይለማሪያም ከፋለ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በክልሉ በ2014/2015 የመኸር የምርት ዘመን 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት በልዩ ልዩ ሰብሎች በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን 4 ነጥብ 6ሚሊየን ሄክታሩ የታረሰ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 4 ሚሊየን ሄክታሩ በዘር ሊሸፈን ችሏል ።
በምግብ ራስን ለመቻል እየተደረገ ላለው ሀገራዊ ጥረት ክልሉ የድርሻውን እየተወጣ ነው ያሉት ሀላፊው፥ በዚህ ምርት ዘመን በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ትላልቅ ክላስተሮችን በማዘጋጀት ስንዴ ብቻ በ1 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ለማልማት መታቀዱን ተናግረዋል ።
በጥቅሉ በምርት ዘመኑ ይገኛል ተብሎ ከሚታሰበው 143 ሚሊየን ኩንታል ምርት ውስጥም 60 በመቶው ስንዴ እደሆነ ነው ዶክተር ሀይለማሪያም የገለፁት ።
በአበበ የሸዋልዑል