አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በነጩ ቤተ መንግሥት የጋዜጠኞች የእራት ግብዣ ላይ የተከፈተው ተኩስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ተመላክቷል፡፡
ኮል ቶማስ የተባለ ግለሰብ ትናንት ምሽት በዋሺንግተን የጋዜጠኞች የእራት ግብዣ ላይ ተኩስ በመክፈት በቁጥጥር ሥር መዋሉን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
የእራት ግብዣው በተካሄደበት ዋሺንግተን ሒልተን ሆቴል እንግዳ የነበረው ተጠርጣሪው ሽጉጥ፣ ቢላ እና ሌሎች መሣሪያዎችን ይዞ እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በወቅቱ ተኩስ ሲከፈት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በደህንነት አባላት ታጅበው በአስቸኳይ ከመድረክ እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን ÷ መርሐ ግብሩም ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡
ጥቃቱ ፕሬዚዳንት ትራምፕን ኢላማ ያደረገ እንደነበር ተኩስ የከፈተው ተጠርጣሪ ለመርማሪዎች መናገሩ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ÷ በምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ፔንሲልቬኒያ ግዛት የተደረገባቸው ግን በቀኝ ጆሯቸው የላይኛው ክፍል ላይ ጉዳት ያደረሰባቸው መሆኑ ይታወሳል፡፡
በብርሃኑ አበራ