Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የተሰረቁ ከ1 ሺህ 200 በላይ የሞባይል ስልኮችና 87 ላፕቶፖች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የተሰረቁ ዕቃዎች ይከማቹባቸዋል በተባሉ ቤቶች ላይ በተደረገ ፍተሻ 69 ተጠርጣሪዎች፣ 1 ሺህ 232 የሞባይል ስልኮች፣ 87 ላፕቶፖችና ሌሎች በርካታ እቃዎች መያዙን ፖሊስ ገለጸ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥናትን መነሻ አድርጎ ባደረገው ኦፕሬሽን÷ በአራዳ፣ በልደታ፣ በቂርቆስ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በየካ፣ በአዲስ ከተማ፣ በአቃቂ ቃሊቲ እና በቦሌ ክፍለ ከተሞች የተሰረቁ  ዕቃዎች ይከማቹባቸዋል በተባሉ ቤቶች ላይ በተደረገ ፍተሻ በተለያየ ጊዜ የተሰረቁ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ እና የመኪና ዕቃዎች ከነ ተጠርጣሪዎቹ መያዛቸውን በአዲስ አበባ ፖሊስ  ልዩ ልዩ እና የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር አለማየሁ አያልቄ ተናግረዋል፡፡

ፍተሻ ከተደረገባቸው 82 ቤቶች ውስጥ 1 ሺህ 232 የሞባይል ስልኮችን ጨምሮ 87 ላፕቶፖች፣ ኮምፒውተር ፣ የመሰረተ ልማት ኬብሎች፣ 231 ስፖኪዮ፣ 3 ቴሌቪዥን፣ 6 ፕሌይ ስቴሽን፣ 1 ወታደራዊ ሬዲዮ እና ሌሎች በርካታ የተለያዩ የመኪና እቃዎች መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ 69 ተጠርጣሪዎች እና ኤግዚቢቶች በሕግ አግባብ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቅሰው÷ፖሊስ በከተማዋ የሚፈፀሙትን የስርቆት እና ሌሎች ወንጀሎች ለመከላከል የጀመረውን ስራ በማገዝ ተባባሪ ለሆኑ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የወንጀል ተግባራትን ለመከላከል የነዋሪው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ረዳት ኮሚሽነሩ÷ሕብረተሰቡ  ከጸጥታ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ንብረት የተሰረቀባቸው ግለሰቦች በተጠቀሱት ክፍለ ከተሞች ቀርበው ንብረታቸው መኖሩን በማረጋገጥ መውሰድ እንደሚችሉ መናገራቸውንም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.