በመዲናዋ የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋ ተመን ከሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ ይተገበራል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋን ለመተመን የተጠናው ጥናት ግኝት ከሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የ2019 ዓ.ም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መወሰኛ ጥናት የፓናል ውይይት በዛሬው ዕለት አካሂዷል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ቅድስት ወ/ጊዮርጊስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው ውል ለ2 ዓመት እንደሚያገለግል ጠቁመው፥ አዋጁ አንድ ተከራይ አንድ ቦታ ላይ ቢያንስ ለሁለት ዓመት ተረጋግቶ እንዲቆይ ያስችላል ብለዋል፡፡
በየዓመቱ በሚከናወነው የዋጋ ጥናት መሰረት የዋጋ ማሻሻያዎች የሚደረጉ ሲሆን፥ በአዋጁ መሰረት የ2019 የቤት ኪራይ የዋጋ ተመን ጥናት መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
የኪራይ ተመን ጥናቱ የተከራዮችን የመክፈል አቅም ባገናዘበና የአከራዮችን ገቢ በማይጎዳ መንገድ ሁሉንም ክፍለ ከተሞች ታሳቢ በማድረግ መከናወኑን አመልክተዋል፡፡
የውል እድሳቱ በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ እንደሚከናወን ገልጸው፥ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመሄድ መዋዋል እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ